በትግራይ የተጠያቂነት ስርዓት የሚያጎለብት ኮንፍረንስ እየተካሄደ ነው

53
መቀሌ ሚያዝያ 27/2010 በትግራይ ክልል የመንግስትን ሀብትና ንብረት አለአግባብ እንዳይባክን የመከላከልና የተጠያቂነት ስርዓት የሚያጎለብት  ኮንፍረንስ በመቀሌ ከተማ  እየተካሄደ ነው፡፡ የክልሉ ዋና ኦዲተር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ረዳኢ በርሄ በኮንፍረንሱ ላይ እንዳሉት መስሪያ ቤታቸው ባለፈው ዓመት በ18 የመንግስት ተቋማት ባደረገው ልዩ የክዋኔና ሂሳብ  ምርምራ ከ17 ሚሊዮን  ብር በላይ ተጭበርብሮ መገኘቱን አረጋግጧል። አለአግባብ ከጠፋው ገንዘብ በተጨማሪ  ከግዥ መመሪያና ከአሰራር ውጭ ክፍተቶች እንዳሉ በምርመራ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡ ከግዥ መመሪያ ውጭና ባልተሟላ ማስረጃ የተከፈለ እንዲሁም በወቅቱ ያልተወራረደ ሂሳብ በምርመራው ወቅት መገኘቱን ኃላፊው አስረድተዋል። በክልሉ ገጠር አካባቢዎች ለወጣቶች ለመኖሪያ ቤት መስሪያ በተሰጣቸው 980 የይዞታ ማረጋገጫዎች ቦታዎች ላይ በተካሄደው የዳሰሳ ጥናትም 112 ህግና ደንብ ባልተከተለ መልኩ እንደተሰጠ ማረጋገጣቸውን አመልክተዋል፡፡ በመሬት አስተዳደርና ልማት የከፋ ችግር ካታየባቸው ከተሞች ውስጥ  የዓድዋ ፣ የሽሬእንዳስላሴና የአላማጣ ከተሞች ተጠቃሽ መሆናቸውን የክልሉ ዋና ኦዲተር ጽህፈት ቤት ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡ በመንግስትና በህዝብ ሃብት ላይ ብክነት  የፈጠሩ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ጉዳያቸው  ወደ ህግ እንዲመራ መደረጉንም አውስተዋል፡፡ የተጠያቂነትን አሰራር ለማጎልበት ጥብቅ መደበኛና ልዩ ክዋኔና ሂሳብ ምርመራዎች አጠናክረው መቀጠላቸውንም ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡ በክልሉ እቅድና ፋይናንስ  ቢሮ የገበያ ጥናት ባለሙያ አቶ ገብረስላሴ ስዩም በበኩላቸው  "በየደረጃው ያሉት አመራሮች ለመንግስት ሃብትና ንብረት የሚያደርጉት ቁጥጥር አነስተኛ ነው "ብሏል። በየደረጃው የሚገኙ አብዛኛዎቹ አመራሮች የመንግስትን የፋይናንስ ግዥ ስርዓት  እንደሚጥሱ ያመለከቱት ባለሙያው የመንግስት ንብረትና ሃብት መሆኑን ተረድቶ ተገቢውን ቁጥጥርና እንክብካቤ እንዲያገኝ  የሚያደርግም ውስን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህንን ክፍተት በመስክ  ምልከታ መረጋገጣቸውን ጠቁመዋል። የክልሉ ምክርቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ  ኮንፍረንሱን ሲከፍቱ "የያዝነውን የልማትና የዲሞክራሲ ግንባታ ቀጣይነት እንዲኖረው  ሙስና እና ብልሹ አሰራር የማይሸከም ትውልድ መገንባት አለብን" ብለዋል፡፡ በክልሉ ያለውን ውስን ሀብት   የህዝቡን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ለታለመለት ዓላማ  ማዋል እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ የተጠያቂነት ስርዓት ለማጎልበት ደግሞ  በየደረጃው የሚገኙ የህዝብ  ምክር ቤቶች  ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡፡ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕርግ የክልሉ ንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አዲስአለም ባሌማ በበኩላቸው " የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለማጎልበት የግልፅነትና የተጠያቂነት ስርዓት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል "ብለዋል፡፡ በየደረጃው  የሚገኙ  አመራሮች ቅንነት በመላበስ  የህዝብ አገልጋዮች መሆናቸው እንዲገነዘቡ የሚያስችል ስራ በቀጣይነት መስራት እንደሚያስፈለግም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም