ጋዜጠኞችና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የግብር አሰባሰቡ ስራው እንዲሳካ የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

54

መቀሌ የካቲት 15/2011 ጋዜጠኞችና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች  የንግዱ ማህበረሰብ ተገቢውን ግብር እንዲከፍል በማነሳሳት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

የትግራይ ክልል ገቢዎች ልማት ባለስልጣን በግብር አሰበሰብ ሂደት ባሉ ችግሮችና መፍትሄ ዙሪያ ከጋዜጠኞችና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ጋር በአዲግራት ከተማ ተወያይቷል።

በውይይቱ ወቅት  የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አሰፉ ሊላይ እንዳሉት፣ ግብር በሚገባ እንዳይሰበሰብ ከሚያደርጉ ችግሮች መካከል የህዝቡ ግንዛቤ ማነስ፣የህግ ማስከበር ስርዓት መላላት፣የግብር ስወራ ይገኙበታል።

" ግብርን በአግባቡ ተሰብስቦ ለሃገር ልማት እንዲውል መላው ህዝብ መነሳሳት አለበት" ብለዋል፡፡

ወይዘሮ አሰፉ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት የቅንጅት ማጣትና ህዝቡን በማነሳሳት ከፍተኛ ሚና ያላቸው ጋዜጠኞችና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ሚናቸውን በተገቢው እንዳልተወጡ ጠቅሰዋል።

" ግብር የመሰብሰብ ስራ መታየት ያለበት ከሃገር ልማትና ከህብረተሰብ ቀጥተኛ ተጠቃሚነት ጋር ነው " ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ በግብር አሰባሰብ ላይ የህዝቡ ተሳትፎና በግብር ስወራ ላይ የሚፈጸሙ ህገ ወጥ ድርጊቶችን  የማጋለጥ ስራን የሚያጎሉ ፕሮግራሞችና መልዕክቶች ማንጸባረቅ እንደሚገባ አመለክተዋል።

በተለይ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ጋዜጠኞች በቁጥር የተሰበሰበው የግብር ገቢ መረጃ እንጂ ከማን እንደተሰበሰበ ፣ፋይዳውን፣ በሂደት የነበሩ ጥንካሬዎችና ድክመቶችን ፣ የህዝብ   ተሳትፎና ፍትሃዊነት  እንዴት እንደነበር ስለማያብራሩ መልዕክቶቹ ትርጉም የለሽ እንደሆኑ ገልጸዋል።

ጋዜጠኞችና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የግብር አሰባሰቡ ስራው እንዲሳካ ዜናና  ፕሮግራሞቹ ትርጉም ባላቸው መልኩ በመስራት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

በባለስልጣኑ የትምህርትና ስልጠና አገልግሎት የስራ ሂደት ባለሙያ አቶ ሙሉብርሃን ኃይለማሪያም በበኩላቸው፣" የግብር አሰባሰብ ሂደት ከአጠቃላይ የሃገሪቱ ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትና ሁኔታ ጋር መታየት አለበት "ብለዋል።

ግብር የመሰብሰብ ጉዳይ የአንድን ሃገር ህዝብ በነጻነት የመኖር ህልውና የማረጋገጥና ቀጣይነት ያለው ልማት እንደሆነ ተናግረው በስራ ሂደት የሚታዩትን ችግሮች በመቀራረብና በቅንጅት በመፍታት ስኬትን ማምጣት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የክልሉ መስተዳድር ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ አቶ ሰሎሞን ገብረመድህን በሰጡት አስተያየት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የግብር መሰብሰብ ስራ ለአንድ አካል  ብቻ የሚተው  ባለመሆኑ በዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት  በሚደረገው ጥረት የበኩሉን  አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የገለጸው ደግሞ የድምጸ ወያኔ  ትግራይ ራዲዮ ጣቢያ ጋዜጠኛ ወልደስላሴ አማረ ነው፡፡

የክልሉ ገቢዎች ልማት ባለስልጣን በተየዘው የበጀት ዓመት ከአራት ቢሊዮን  700  ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ በግማሽ ዓመቱ ከሁለት ቢሊዮን  400 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ መከናወኑን ቀደም ሲል ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም