በሰሜን ወሎ ዞን የተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት ውጤታማ አልሆነም

59

ወልዲያ  የካቲት 15/2011 በሰሜን ወሎ ዞን የተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት ውጤታማ አለመሆኑን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው አለመስራታቸውና የበጀት እጥረት ውጤታማ ላለመሆኑ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።

በዞኑ ትምህርት መምሪያው የጎልማሶች ትምህርት ባለሙያ አቶ ደሳለኝ አስፋው ለኢዜአ እንደገለጹት የጎልማሶች ትምህርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀዛቀዘ መጥቷል፡፡

በዘንድሮ ዓመት 72ሺህ ጀማሪ ጎልማሶችን ለማስተማር በታቀደው መሰረት 62 ሺህ ሰዎችን ለይቶ የመመዝገብ ሥራ ቢከናወንም ወደ ትምህርት የገቡት አምስት ሺህ 500 ያህሉ ብቻ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ መማር ካለባቸው 55 ሺህ የሚጠጉ ጎልማሶች መካከልም እየተማሩ የሚገኙት 5 ሺህ የሚጠጉ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ለዚህም የትምህርት፣ የግብርና፣ የጤናና መሰል ባለድርሻ ተቋማት ተቀናጅተው አለመስራት መሰረታዊ ችግር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከእዚህ በተጨማሪ የመማር ማስተማር ስራውን የሚደግፍ በቂ በጀት አለመመደብ ሌላው ምክንያት መሆኑን አመልክተው በተለይ ዘንድሮ የአመቻቾች የኩንትራት ቅጥር መከልከሉ ችግሩ እንዲባባስ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይ የተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት በቅድመ መደበኛ ትምህርት ስር ተካቶ መተግበር ካልተቻለ ትምህርቱ ውጤታማነቱ ይበልጥ አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የዞኑ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ የሒሳብ ሹም አቶ ተስፋ መላኩ በበኩላቸው የኮንትራት ቅጥሩ በክልሉ መንግስት የተከለከለ ቢሆንም ወረዳዎች በውስጥ ገቢያቸው መሸፈን የሚችሉበት አግባብ መኖሩን አመልክተዋል፡፡

የጉባላፍቶ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ ብርሃኑ በበኩላቸው በተያዘው በጀት ዓመት 15 ሺህ ጎልማሶችን ተቀብሎ ለማስተማር ጥረት ቢደረግም በበጀት እጥረት ምክንያት ትምህርቱን መስጠት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

የተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት በየደረጃው ባለው አመራር ምንም አይነት ትኩረት እንዳልተሰጠው የገለጸው ደግሞ በጋዞ ወረዳ የስታይሽ የጎልማሶች ጣቢያ አመቻች ወጣት ማስሬ ቦጋለ ነው፡፡

"በተለይ የቀበሌ አመራሩ ድጋፍ ስለማያደርግ በራሳችን ቤት ለቤት ቀስቅሰንና አስተምረን ኃላፊነታችንን ለመወጣት አልቻልንም" ብሏል፡፡

ዘንደሮ ከህዳር ወር ጀምሮ አስክሁን ምንም ክፍያ ሳይሰጣቸው በተስፋ ጎልማሶችን በማስተማር ላይ መሆናቸውንም አመቻቹ ተናግሯል፡፡

የእዚሁ ጣቢያ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ የሆኑት ጎልማሳ አርሶ አደር ወንድምነው ጫኔ በበኩላቸው በጎልማሶች ትምህርት በመሳተፍ ማንበብና መጻፍ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

የጎልማሶች ትምህርት ዓላማ በመደበኛው ትምህርት ቤት ገብተው መማር ያልቻሉ ጎልማሶች ማንበብ፣ መጻፍና ማስላት እንዲችሉ ከማድረግ ባለፈ በተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችንና በጤና አጠባበቅ ላይ ግንዛቤያቸውን ማሳደግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከ100 ሺህ በላይ ጎልማሶችን ማስተማር እንደተቻለም ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም