የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለማሳደግ በዘርፉ የተሻለ ስምና ተሞክሮ ካላቸው አገሮች ጋር መስራት ያስፈልጋል ተባለ

75

አዲስ አበባ የካቲት 15/2011 የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለማሳደግ በዘርፉ የተሻለ ስምና ተሞክሮ ካላቸው አገሮች ጋር የትብብር ግንኙነት መፍጠር እንደሚገባ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ተናገሩ።

አሰልጣኝ አብራሃም እንዳሉት በስፖርት የውጭ ግንኙንት ዲፕሎማሲ በመፍጠር የአገሪቷን የስፖርት እድገትና ተሳትፎ ማጠናከር ያስፈልጋል።

የኢትዮጵያን እግር ኳስ አሁን ካለበት ዝቅተኛ ደረጃ ከፍ ለማድረግም ስፖርቱን መሰረት ያደረገ የውጭ ዲፕሎማሲ ስራ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  ከሌሎች አገሮች ጋር አብሮ ለመስራት የጀመራቸው ውጥኖች እንዳሉ በመጥቀስ በጎ ጅምር መሆኑንም አንስተዋል።

ብሄራዊ ቡድኑ ወደ ዓረብ አገሮች በመሄድ ልምምድ እንዲሰራ ለማድረግ ከኳታር እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ንግግር መጀመሩንም ገልጸዋል።

"ከአገር ውጭ ተጫዋቾች ልምምድ ሲሰሩ ሙሉ ትኩረታቸውን ለኳሱ ሰጥተው እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል" ያሉት አሰልጣኙ ጅምሩ የሚበረታታ ነው ሲሉም አድንቀዋል።

የቴክኒክ፣ የታክቲክና ሌሎች ሞያዊ ድጋፎችን ለማግኘት ከጃፓን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ንግግር መጀመሩም ተጨማሪ እድል ሊፈጥር እንደሚችል ተስፋ አድርገዋል።

ከዚህ ባለፈ በእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድኑ ተጫውተው ያለፉ ተጫዋቾች ያላቸውን ልምድ እንዲያካፈሉ ለማድረግ የሚያስችል አሰራር መጀመሩንም አሰልጣኙ ገልጸዋል።

ይህ አሰራር የቀድሞ ተጨዋቾች ያላቸውን የካበተ ልምድ ለትውልድ እንዲያስተላልፉ ለማድረግ እንዲሁም በስፖርቱ በባለቤትነት ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ጠቀሜታ እንዳለውም አንስተዋል።

የቀድሞ ተጨዋቾች ልምድና ተሞክሯቸውን ከማጋራት ባለፈ በያሉበት አካባቢ ስፖርተኞችን በመመልመል እንዲያግዙ ያደረጋልም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም