ጨፌው የህግ የበላይነትን በማስከበርና ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ዙሪያ ይመክራል

98

አዲስ አበባ የካቲት 15/2011ጨፌው በዋናነት የህግ የበላይነትን በማስከበርና ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚመክር ገለጸ።

የጨፌ ኦሮሚያ 5ኛ የጨፌው የስራ ዘመን፣ 4ኛ ዓመት  9ኛ መደበኛ ጉባኤ መካሄድን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ጉባኤው በዋናነት የህግ የበላይነትን አጠናክሮ በማስከበርና ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ዙሪያ እንደሚመክር ገልጿል።

ጨፌው ባለፈው በጀት ዓመት መጨረሻ ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ጉባዔው በጨፌው ክትትልና ግምገማ ሲካሄድባቸው የቆየው የዋና ኦዲተር እና የሶስቱም የመንግስት አካላት የስራ አፈጻጸም ቀርቦ በሰፊው ከመከረበት በኋላ ማጽደቁ ይታወሳል።

የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የፊታችን የካቲት 19 እና 20 የሚካሄደው የጨፌው ጉባኤ በዋናነት ትኩረቱን አድርጎ የሚወያየው የህግ የበላይነትን ማስከበርና ሰላምን በዘላቂነት የማስፈን ተግባር ላይ ነው ብለዋል።

ሌላው በጉባኤው ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ከፕሮጀክቶች ጋር ተያይዞ ያሉት ክፍተቶች ሲሆን፣ ተጀምረው ባላለቁና የተጠናቀቁ ፕሮጀቶችንም በተመለከተ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚወያዩበት ወይዘሮ ሎሚ ገልጸዋል።

ህዝቡ ከረጅም ጊዜ አንስቶ ሲያነሳቸውና መንግስትም ለመመለስ ጥረት ሲያደርግባቸው የቆዩ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችም በጨፌው ትኩረት ተሰጥቶ ለውይይት ከሚቀርቡ ጉዳዮች አንደኛው መሆኑን አንስተዋል አፈ ጉባዔዋ።

በተጨማሪም በጨፌው ሹመቶች የሚደረጉ ሲሆን ተሿሚዎቹም ጨፌውና ህዝቡ አመኔታ የጣለባቸው፤ ከዚህ በፊት ከነበረው አሰራር በበለጠ ከህዝብ ጋር ተቀራርበው የሚሰሩ ሲሆኑ አብዛኛዎቹ ተሿሚዎች የፍርድ ቤት ዳኞች መሆናቸውም ተገልጿል።

ከህብረት ስራ ማህበር ኤጀንሲ ጋር  ተያይዞ የተዘጋጀ አዋጅ መኖሩን የገለጹት አፈ ጉባዔዋ፤  የኤጀንሲው ሃላፊነትና የስራ ድርሻ ጋር ተያይዞና በስራ ላይ እየገጠሙት ያሉትን ክፍተቶች ለመፍታት በሚረዱ ጉዳዮች ላይ ጨፌው መክሮ የሚያጸድቅ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም