በመቀሌ ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት የሰላም ኮንፈረንስ ሊካሄድ ነው

88

መቀሌ የካቲት 15/2011 በመቀሌ ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት ምሁራንን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የሰላም ኮንፈረንስ ሊካሄድ ነው።

በዩኒቨርስቲው የህብረተሰብ ቋንቋዎች ኮሌጅ አስተባባሪነት የሚካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ በትግራይ ና አማራ ክልል  መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር  በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ እንደሚመክር የኮሌጁ ዲን ዶክተር ገብረእየሱስ ተክሉ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የአማራ ክልል ተወላጅ  ምሁራን፣የኃይማኖት መሪዎችና የሃገር ሽማግሌዎች ከትግራይ ክልልም በተመሳሳይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ይሳተፋሉ።

በኮንፈረንሱ በተለይም ተመሳሳይ የሆነ ባህል፣ቋንቋና ኃይማኖት እና እምነት ያላቸው የሁለቱም ክልሎች ህዝቦች ያለባቸውን ችግር ተነጋግረው በመፍታት ዘላቂ ሰላማቸውን ለማረጋገጥ የሚመቻቹበት አካሄድ እንደሚሆን ዶክተር ገብረእየሱስ ተናግረዋል።

" ሰላምን ማረጋገጥ የምሁራን ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ህብረተሰብ ኃላፊነት ነው" ያሉት ዲኑ፣በኮንፈረንሱ የሚሳተፉ አካላት የሰላም መልእክተኛ ሆነው የሁለቱን ክልሎች ግንኙነት ለማጠናከር ኃላፊነት እንዲወስዱ መነሳሳትን የሚፈጥርበት  ጭምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዶክተር ገብረእየሱስ እንዳሉት በኮንፈረንሱ በምሁራኑ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ይቀርባሉ፤ በተለይ ሁለቱን ህዝቦች የሚያገናኟቸው በርካታ መልካም እሴቶች እንዳሉና ይህንን በማጎልበት ችግሮቻቸውን በጋራ ተነጋግረው  እንዲፈቱ መነቃቃትን ለመፍጠር ዓላማ ያደረገ ነው።

ችግሮችን ለመፍታት የሰላም አማራጭ ዋንኛ መንገድ እንደሆነ አመልክተው "በህዝቦቹ መካከል ሰላምን እንዲደፈርስ የሚያደርጉ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አማራጮችን የሚያስቀምጥ ይሆናል"ብለዋል።

ኮንፍረንሱ የሰላም መንገዱ ቀጣይነት እንዲኖረውም ዩኒቨርስቲዎች በምርምርና ጥናት ላይ የተመሰረቱ የመፍትሄ መንገዶችን ለማፈላለግ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው።

በመጪው ቅዳሜና እሁድ በሚካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ እስከ 500 የሚደርሱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም