የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮናን ለማስተናገድ አብዛኛው ዝግጅት ተጠናቋል - የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን

111

አዲስ አበባ የካቲት 15/2011 14ኛውን የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና ለማስተናገድ አብዛኛው ዝግጅት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ብስክሌት ፌዴሬሽኑ በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ከመጋቢት 5 እስከ 10 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው ሻምፒዮና ዙሪያ በስፖርት ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ትላንት ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በሻምፒዮናው ላይ ከ35 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ከ400 እስከ 450 ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎም ይጠበቃል።

የግል ሰዓት ሙከራ፣ የቡድን የሰዓት ሙከራ፣ የጎዳና ላይ ውድድርና በሻምፒዮናው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የብስክሌት የቅብብል ውድድር (Mixed Relay Competition) በሁለቱም ጾታዎች በታዳጊና አዋቂ ዘርፎች ይካሄዳሉ።

ነሐሴ 26 ቀን 2010 ዓ.ም የአፍሪካ ብስክሌት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር ሞሐመድ ዋጊህ አዛም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት አገሪቷ 14ኛውን የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና እንደምታስተናገድ በይፋ መገልጻቸውና የሻምፒዮናው አዘጋጅነት አርማ ማስረከባቸው ይታወሳል።

በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ የሻምፒዮናውን አዘጋጅነት ከተረከበች ስድስት ወራት ተቆጥረዋል።

ኢትዮጵያ አዘጋጅነቱን ከተረከበችበት ጊዜ አንስቶ በመንግስት በኩል በቂ ዝግጅት ሲደረግ እንደነበረም የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወርቁ ገዳ ገልጸዋል።

ውድድሩን ለማስተናገድ የሚያስችሉ ስራዎች ለማከናወንም የውድድር፣ የቴክኒክና መስተንግዶ፣ የሎጅስቲክ፣ የጤናና ጸጥታ ኮሚቴዎች ተዋቅረው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሆቴል፣ የትራንስፖርት አቅርቦት፣ ለውድድሩ የሚያስፈልገውን ቦታ የመምረጥ፣ የማዘጋጀትና ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎች መጠናቀቃቸውንም አመልክተዋል።

ቀሪ ስራዎች ሻምፒዮናው አንድ ሳምንት ሲቀረው ለውድድር የተዘጋጁ መንገዶችን ዝግ የማድረግና ውድድሩ ሲካሄድ ያሉ ተግባራት መሆኑንና የዝግጅት ስራው በአብዛኛው ተጠናቋል ማለት እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

መንግስት ለሻምፒዮናው ዝግጅት 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በጅቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው እስከ ሻምፒዮናው መጨረሻ ድረስ ለሚከናወኑ ተግባራትም ከተጠቀሰው ብር በላይ ሊጨምር እንደሚችል ነው አቶ ወርቁ ያስረዱት።

በጀቱ የተገኘው ከስፖርት ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴና ከአማራ ክልል መንግስት እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለውድድሩ ተሳታፊዎች የአየር ትኬት ዋጋ ከ12 እስከ 15 በመቶ ቅናሽ እንደሚያደርግ ገልጸው ይሄም ብዙ ተወዳዳሪዎች እንዲሳተፉ የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ብስክሌት ኮንፌዴሬሽንና የዓለም አቀፉ የብስክሌት ማህበር ለኢትዮጵያ የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያድርጉና ከሻምፒዮናው ጎን ለጎን ለብስክሌት ተወዳዳሪዎችና የጥገና ባለሙያዎች ስልጠና እንደሚሰጡም ጠቁመዋል።

በብስክሌት ፌዴሬሽኑ ከተመለመሉት የትግራይ፣ አማራ፣ ደቡብና ኦሮሚያ ክልሎችና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የአማራ ክልል መስፈርቶቹን አሟልቶ በመገኘቱና ዝግጁ በመሆኑ ሻምፒዮናውን ባህርዳር ለማድረግ ውሳኔ ላይ መደረሱንም አብራርተዋል።

የአፍሪካ ብስክሌት ኮንፌዴሬሽን ሻምፒዮናው በአዲስ አበባ እንዲዘጋጅ ፈልጎ የነበረ ቢሆንም ለስድስት ቀናት መንገድ ዘግቶ ማከናውን በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ ከመዲናዋ ውጪ እንዲካሄድ መደረጉንም አመልክተዋል።

በአዳማ ከተማ በታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም በተካሄደ የብሔራዊ ቡድን መምረጫ ውድድር ከ190 በላይ ተወዳዳሪዎች ተሳትፈው ከነዚህ ውስጥ የተሻለ ውጤት ያመጡ 35 ብስክሌተኞች ለብሔራዊ ቡድኑ መመልመላቸውንም አክሎዋል።

በዚሁ መሰረት ብስክሌተኞቹ ከአንድ ሳምንት በፊት በትግራይ ክልል ሽሬ ከተማ ልምምድ እያደረጉ እንደሚገኙና ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ውድድሩ ወደ ሚካሄድበት ባህርዳር ከተማ አቅንተው ልምምድ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

ተወዳዳሪዎቹ የተመረጡበት መስፈረትም ወቅታዊ ብቃት እንደሆነና ከተመለመሉት ተወዳዳሪዎችም በተለያዩ የአፍሪካና የአውሮፓ ከተሞች በሚገኙ የብስክሌት ተወዳዳሪዎች እንደሚገኙበትም ጠቅሰዋል።

ባለፈው አንድ ወር ለሻምፒዮናው ዝግጅት ይረዳ ዘንድም ተወዳዳሪዎቹ በካሜሮንና ጋቦን በተካሄዱ የብስክሌት ቱሮች ላይ እንዲሳተፉ መደረጉንም አብራርተዋል።

ሻምፒዮናው እ.አ.አ በ2020 በቶኪዮ በሚካሄደው 32ኛው የኦሎምፒክ ውድድር ተሳታፊዎች የሚለዩበት የማጣሪያ ውድድር በመሆኑ ጠንካራ ፉክክር እንደሚኖርም በመገንዘብ ጠንካራ ዝግጅት እየደተረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ከ35ቱ ተወዳዳሪዎች ውጪ በአውስትራሊያው የብስክሌት ክለብ ሚቼልቶን-ስኮት ክለብ የሚገኘው ጽጋቡ ገብረማርያም የመሳተፉ ጉዳይ ክለቡ በተያዘው ወር ላይ በአውሮፓ በሚካሄድ የብስክሌት ውድድር ላይ ይሳተፋል ወይስ አይሳተፍም በሚለው ጉዳይ የተንጠለጠለ ነው ብለዋል።  

ጽጋቡ እ.አ.አ በ2016 በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ በተካሄደው 31ኛው የኦሎምፒክ ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ መሳተፉንም አስታውሰዋል።

በአጠቃላይ በብሔራዊ ቡድኑ ተወዳዳሪዎችን ጨምሮ እስከ 50 ልዑካን እንደሚኖሩም ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮናው በኢትዮጵያ መዘጋጀቱ የብስክሌት ስፖርት በኢትዮጵያ እንዲጎለብትና ስፖርቱ እንዲስፋፋ ለማድረግ የሚያችስሉ የንቅናቄ ስራዎችን ለመስራት፣ተተኪ ብስክሌተኞችን ለማፍራትና ለአገር ገጽታ ግንባታ ያለው ፋይዳ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ሻምፒዮናውን አስመልክቶ የተዘጋጀው ድረ ገጽ ነገ ወይም ከነገ በስቲያ ይፋ እንደሚደረግም አክለዋል።

ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በሩዋንዳ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ በተካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና በ3 ወርቅ በ7 የብርና በ3 የነሐስ በድምሩ 13 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ኤርትራን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል።

የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና ከ 2005 እ.አ.አ ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኝ ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም