የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የሚሰጡ ኅብረት ሥራ ማህበራትን ማቋቋም የሚያስችል የአዋጪነት ጥናት ተጀመረ

62

አዲስ አበባ የካቲት 14/2011 የአፍሪካ ልማት ባንክ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የሚሰጡ ኅብረት ሥራ ማህበራትን ማቋቋም የሚያስችል የቢዝነስ ሞዴል የአዋጪነት ጥናት በኢትዮጵያና በናይጄሪያ ማካሄድ ጀመረ።

የተጀመረው ጥናት እ.አ.አ በ 2025 የኤሌክትሪክ አቅርቦትን በአፍሪካ ተደራሽ ለማድረግ የተቀመጠው የባንኩ ግብ አንድ አካል እንደሆነም ተገልጿል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ አለመሆን የአህጉሪቱን ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት በዓመት ከ2-4 በመቶ እንዲቀንስ እንዲሁም የስራ ፈጠራና የድህነት ቅነሳ ስራዎች ወደ ኋላ እንዲጎተቱ እያደረገ መሆኑ ተጠቅሷል።

የአዋጪነት ጥናቱ በደቡብ ደቡብ የትብብር ትረስት ፈንድ የሚደገፍ ሲሆን ብሔራዊ የገጠር ኤሌክትሪክ ኅብረት ሥራ ማኅበር የጥናት ስራውን እንደሚሰራ ተገልጿል።

ማኅበሩ በሁለቱ አገራት የኤሌክትሪክ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የሚያጋጥሙ የሕግና ደንብ፣ የቴክኒክ እንዲሁም የማህበረ ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎችን እንደሚያጤን ባንኩ አመልክቷል።

የዚህ አይነቱ አገልግሎት በተለያዩ አገራት የሚተገበር ሲሆን የገጠሩን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ በግሪድ ወይም ኔትወርክ ማስፋፊያና ህብረት ስራ ማህበራት ይተገበራል።

አገልግሎቱ ውጤታማ በሆነባቸው አካባቢዎች የገጠር ኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን በማሳደግ ቀጣይነት ያለው የንግድ ስራ እውን እንዲሆን አስችሏል።

ባለፈው ሐምሌ 2018 ‘አፍሪካ ኢነርጂ ማርኬት ፕሌስ’ በሚል ርዕስ በተካሄደ ጉባኤ የኢትዮዽያና ናይጄሪያ የኢነርጂ ሚኒስትሮች አገራቸው የገጠር የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማሻሻል ቁርጠኛ መሆናቸውን በመግለጻቸው ዕድሉ እንደተሰጣቸው ዘ ቴሌግራፍ የልማት ባንኩን የፓወር ሲስተም ዲቨሎፕመንት ዳይሬክተር ባቺ ባልዴህን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም