በኢትዮጵያ ረጅም ዓመታት ላገለገሉ መምህራን እውቅና እና ሽልማት ተሰጠ

56

አዲስ አበባ  የካቲት 14/2011 በኢትዮጵያ ረዥም ዓመታት ላገለገሉ መምህራን እውቅናና ሽልማት ተሰጠ።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር 70ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።

በዚሁ ወቅትም በመምህርነት ረጅም እድሜ ያሳለፉ 19 የእውቀት አባቶች የወርቅ ሜዳልያ፣ የምስክር ወረቀትና የገንዘብ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።

ሽልማቱ የተበረከተላቸው መምህራን ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ፣ ከአገልግሎት ዘመን ባሻገር በሙያ ትጋታቸውና በስነ-ምግባራቸው ለትውልድ ምሳሌ ለመሆን የሚያሰቸለ የላቀ አፈፃፀም ያላቸው በመሆናቸው ነው። 

በሽልማቱ ከኦሮሚያ አራት፣ ከአማራ ሶሰት፣ ከደቡብ ሁለት፣  ከአዲስ አበባ ሁለት፣ ከትግራይ ሁለት፣ ከሃረሪ አንድ፣ ከቤኒሻልጉልጉምዝ አንድ፣ ከጋምቤላ አንድ፣ ከሱማሌ አንድ፣  ከድሬደዋ አንድ እና  ከአፋር አንድ መምህራት ተሸላሚ ሆነዋል። 

ከተሸላሚዎቹ መካከል ከ35 አስከ 40 ዓመት በመምህርነት ያገለገሉ ይገኙበታል።

መምህራኑም የተሰጣቸው ሽልማትና እውቅና በሙያቸው የበለጠ እንዲተጉ፣ ትውልድ የመቅረፅ ኃላፊነታቸው እዲጨምር አቅም እንደሚሆናቸው ተናግረዋል።

ከተሸላሚዎቹ መካከል የሀረሪ ክልሉ 'ጀግኖች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህረት ቤት' መምህርት ስመኝ ተሰማ፣  የሀዋሳ ከተማ ታቦር መሰናዶ ትምህርት ቤት መምህር ቦርሳሞ ቦሎሎ እና  በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ከተማ ሃይለማሪያም ማሞ መሰናዶ ትምህርት ቤት መምህር ወንደሰን ተሰማ፣ ይገኙበታ።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ባሰሙት ንግግር፣ መምህራን በመማር ማስተማሩ ሂደት የትምህርት ጥራትና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ ያላሳለሰ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልፀዋል።

"መምህራንለዘመናት በብዙ ውጣ ውርድ ውስጥ አልፈው ትውልድን የሚያነጹና  በብዙ ችግር ውስጥ ሆነው አገራቸውን የሚያገለግሉ የእውቀት መሰረት በመሆናቸው እውቅና ሊቸራቸው ይገባል" ሲሉም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ዮሃንስ በንቲ በበኩላቸው፣ ማህበሩ ከተቋቋበት አላማ በመነሳት ጥራት ያለው ትምህርትን ለሁሉም ዜጋ ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የማህበሩ አባላትን መብትና ጥቅም ለማስከበር  ማህበሩ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል። ማህበሩ እያጋጠሙት ያሉትን ፈተናዎች በመጋፈጥና ደረጃ በደረጃ እየፈታ አሁን የተሻለ ቁመና ላይ  እንደሚገኝም ተናገረዋል።

በአሁኑ ወቅት በመላው ኢትዮጵያ 670 ሺህ መምህራን በሥራ ላይ ናቸው።

የዛሬ 70 ዓመት በ1941 ዓ.ም የተመሰረተው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር  ከ508 ሺህ የሚልቁት አባላት አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም