በደብረ ብርሃን ከተማ የንግድ ትርኢትና ባዛር ተከፈተ

84

ደብረ በርሃን የካቲት14/2011 በደብረ ብርሃን ከተማ 250 የሃገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ነጋዴዎች የተሳተፉበት የንግድ ትርኢትና ባዛር ተከፈተ፡፡

" ፍቅር ሰላም ደብረብርሃን 2011" በሚል ዛሬ የተከፈተው የንግድ ትርኢትና ባዛር ለ12 ቀናት እንደሚቆይ ተመልክቷል።

የደብረብርሃን ከተማ ዘርፍ ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አማረ ገብረጊዮርጊስ እንዳሉት ባዛሩ ነጋዴዎችና በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ አምራቾች ተሳትፈዋል፡፡

ከተሳታፊዎቹ መካከልም 40 የሚሆኑት ከህንድና ከቱርክ የመጡ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ከአዲስ አበባና ከሌች ከተሞች የመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"ባዛሩ የገበያ ትስስር ከመፍጠሩም በላይ የአካባቢውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የበለጠ ለማስተዋወቅ ያግዛል" ብለዋል፡፡

እንደ አቶ አማረ ገለጻ የንግድ ትርኢትና ባዛሩ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 12 ቀናት በሚኖረው ቆይታ ከ50 እስከ 80ሺህ ህዝብ ይጎበኘዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢም ለመሰባሰብም ታቅዷል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድም በበኩላቸው እንዳሉት በደብረብርሃንና አካባቢው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እያደገ በመምጣቱ ለንግዱ መነቃቃት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው፡፡

ከኢንቨስትመንት መምጣት ጋር በተያያዘ የአካባቢው ነጋዴዎች ምርጥ ተሞክሮን በመቅሰም በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች መሳተፍ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህ የንግድ ትሪኢትና ባዛር የውጪ ባለሀብቶች በመሳተፋቸው የአካባቢው ነጋዴዎችና በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የተደራጁ ወጣቶች የተሻለ ድልምድ ካላቸው ጋር የግብይት ሰልሰለት መፍጠር እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡

"ብሩክ ተስፋዬ እና ጓደኞቻቸው የቤትና የቢሮ እቃዎች አምራች የሕብረት ሽርክና ማህበር ” ሰብሳቢ ወጣት ብሩክ ጌታቸው በበኩሉ በወጣቶች ፈንድ ባገኘኑት 700 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ ሥራ መጀመራቸውን ተናግሯል፡፡

በባዛሩ መሳተፋቸው ምርቶቻቸውን ከማስተዋወቀ በተጨማሪ ከተለያዩ ነጋዴዎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠርና የተሻለ የንግድ ክህሎት ለመቅሰም እድል ይፍጥርልናል የሚል እምነት እንዳለው ገልጿል፡፡

በንግድ ትርኢቱ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ነጋዴዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የከተማው ነዋሪዎች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም