በባሌ ዞን 60 የማምረቻና የመሸጫ ሼዶች ተነጥቀው ለተተኪ ወጣቶች ተላለፉ

76

ጎባ የካቲት 14/2011 በማይገባቸው አካላት ተይዘው የነበሩ 60 የማምረቻና የመሸጫ ሼዶችን ጨምሮ የማዕድን ማምረቻ ቦታዎች ተነጥቀው ለስራ አጥ ወጣቶች መተላለፋቸውን የባሌ ዞን የስራ ዕድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት አስታወቀ ፡፡

ከተነጠቁት ሼዶች መካከል በኪራይ ለሦስተኛ ወገን ተላልፈው የተሰጡ እንደሚገኙበትም ፅህፈት ቤቱ ገልጿል ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጫልችሳ ዘውዴ ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለፉት ስድስት ወራት የተካሄደን ጥናት መሰረት በማድረግ ሼዶቹና የማዕድን ማምረቻ ቦታዎቹ ተነጥቀው ለሥራ አጥ ወጣቶች እንዲተላለፉ ተደርጓል ።

ጽህፈት ቤቱ ለወጣቶች ሼዶችን ሲሰጥ በአምስት ዓመት ውስጥ ሰርተውባቸው ለተተኪዎች እንዲያስተላልፉ ታሳቢ በማድረግ መሆኑንም ተናግረዋል ።

“በጥናቱ መሰረት ከጊዜ ገደቡ በላይ በወጣቶች ተይዘው የቆዩ፣ ለሦስተኛ ወገን ተከራይተው ባልተገባቸው ሰዎች የተያዙና ከዓላማ ውጭ የባለሀብቶች መጠቀሚያ የሆኑ ሼዶችና የማእድን ማምረቻ ቦታዎች ተነጥቀው በማህበር ለተደራጁ ለተተኪ ስራ አጥ ወጣቶች ተላልፈዋል “ ብለዋል ።

በተመሳሳይ በጎባ ከተማ ከ20 ዓመታት በላይ በተወሰኑ ሰዎች ተይዘው የቆዩ የአሸዋ መሸጫ ቦታዎችም ተነጥቀው ለተደራጁ ወጣቶች መተላለፋቸውን ገልጸዋል ።

በግብርና ሥራ ለተሰማሩ የገጠር ወጣቶችም 900 ሄክታር የሚጠጋ የእርሻ መሬት መሰጠቱን ነው አቶ ጫልችሳ ተናገሩት።

እንደእርሳቸው ገለጻበዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት 10 ሺህ የሚጠጉ ወጣቶች የመስሪያና የመሸጫ ቦታን ጨምሮ ሌሎች ተጓዳኝ አገልግሎቶችን ተጠቃሚ  እንዲሆኑ ተደርጓል ።

ለወጣቶቹ ለመነሻ የሚሆን ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መሰጠቱንም አመልክተዋል።

ወጣቶቹ በተደረገላቸው ድጋፍ በመታገዝ በግብርና፣ በመንገድ ስራ፣ በጥቃቅን ንግድና በአገልግሎት መስኮች መሰማራታቸውንም አመልክተዋል።

የስራ እድል ከተፈጠረላቸው የጎባ ከተማ ወጣቶች መካከል ወጣት አቤል ስዩም  በሰጠው አስተያየት“በከተማው  የተገነቡ  ሼዶች ለበርካታ ዓመታት በተወሰኑ ሰዎች ተይዘው በመቆየታቸው ተተኪዎች ተጠቃሚ እንዳንሆን አድረጎናል” በሚል ለአስተዳደሩ ጥያቄ ሲያነሱ መቆየታቸውን አስታውሷል ።

“አሁን ላይ የተለቀቁ ሼዶች ስለተሰጡን የመስሪያ ቦታ አግኝተናል” ያለው ወጣቱ አስተዳደሩ የወሰደው እርምጃ ለጥያቄያቸው ምላሽ የሰጠ መሆኑን ተናግሯል ።

በጥቃቅን ንግድ የሥራ ዘርፍ ለመሰማራት የቦታ ጥያቄ ካቀረብን አንድ ዓመት ሞልቶናል ያለችው ደግሞ በከተማው ምስራቅ ቀበሌ ነዋሪዋ አልማዝ ከተማ ናት ፡፡

“እኔና ሌሎች ጓደኞቼ አሁን የተሰጠንን ሼድ ሰርተንበት በተሰጠን የጊዜ ገደብ ለሌሎች ወጣቶች ለማስተላለፍ የስነ ልቦና ዝግጅት አድርገናል” ብላለች፡፡

በዞኑ  የስራ ዕድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት መረጃ መሰረት በበጀት ዓመቱ አለአግባብ የተያዙትን ከማስለቀቅ ጎን ለጎን  148  አዳዲስ የመስሪያ  ሼዶችን ሰርቶ ለማጠናቀቅ  በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ታውቋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም