ተፈናቃይ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም ድጋፍ ተጠየቀ

49

ባህርዳር የካቲት 14/2011 በአማራ ክልል ተፈናቃይ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም ህብረተሰቡና ድርጅቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ፡፡

የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ዋና ዳሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ የተፈናቃዮችን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው ዛሬ ለጋዜጠኞች  መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በዚሁ መግለጫቸው እንዳሉት በክልሉ ውስጥ የተፈናቃዮች ቁጥር 90 ሺህ 736 ደርሷል።

በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በነበረው ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች 60 በመቶውን እንደሚሸፈን አመልክተው በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የክልሉ መንግስት ግብረ ሃይል ግብረሃይል አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ  አብዛኛዎቹ በየግለሰቦች ቤት ተጠገተው  እንዳሉ ጠቁመው የተወሰኑት ደግሞ  በ13 ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ አስረድተዋል።

የክልሉ መንግስት በራሱ አቅም ብቻ ችግሩን መፍታት እንደማይችል ያስታወቁት አቶ አሰማኸኝ  ህብረተሰቡና ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ በቀረበው ጥሪ መሰረትም በአጭር ጊዜ ውስጥ 45 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ መቻሉን አመልክተዋል።

ሆኖም ተፈናቃዮችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ፣ባለሀብቱና ድርጅቶች አሁንም  ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳመለከቱት የክልሉ መንግስት በተጨማሪ  በአዲስ አበባ፣ደሴና ጎንደር  የገንዘብ አሰባሰብ  አስተባባሪ ኮሚቴ በመመደብ  ተፈናቃዮችን በታቀደው ጊዜ መልሶ ለማቋቋም እየሰራ ነው። 

ድጋፍ የሚያደርግ አካል በሚቀርበው አካባቢ በተደራጀ አግባብ ለተቋቋመው ኮሚቴ እርዳታውን ማስረከብ ይችላል።

በነበረው ችግር  የተቃጠሉ  መኖሪያ ቤቶች መልሶ ገንብቶ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም የክልሉ መንግስት ከ155 ሺህ በላይ የቤት መስሪያ ቁሳቁስ ለማመቻቸት በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

አቶ አሰማኸኝ ተፈናቃዮችን መልሶ በማደራጀት ተቋማት፣ ባለሃብቶችና ግለሰቦች እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

" ከቤንሻንጉል፣ሶማሌ፣ ኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደነበሩበት አካባቢ ለመመለስ ከክልሎች ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው" ሲሉም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም