አዲስ አበባን እንደስሟ አድርጎ ለትውልድ ለማሸጋገር የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል--ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ

133

አዲስ አበባ የካቲት 14/2011 አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ አድርጎ ለትውልድ ለማሸጋገር የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናገሩ።

ምክትል ከንቲባው የአዲስ አበባን የወንዞችና ወንዝ ዳርቻዎች ማልማት አዲስ ፕሮጀክትን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት "በተራሮች ከፍታ ላይ የምትገኘው አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስ ሆና  ለትውልድ የምትሸጋገር ውብ ከተማ ማድረግ ይገባል" ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መሪነት በከተማ አስተዳደሩ አስተባባሪነትና በከተማዋ ነዋሪዎችና በወጣቶች ትብብር ለትውልድ የሚሸጋገር ድንቅ ከተማ መገንባታችንን እንቀጥላለንም ነው ያሉት ኢንጂነር ታከለ።

ፕሮጀክቱ ለትውልድ የሚተላለፍ የትውልድ አሻራ ያለበትና ሁላችንም የጋራ እሴቶቻችንን የምናስተላልፍበት በመሆኑ ልንደሰት ይገባልም ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ከተማዋ እንደስሟ እንድትኖር ወንዞችና የወንዞች ዳርቻዎች ሁሉ የቆሻሻ መናኸሪያ ሳይሆኑ የሰው ልጅ በተለይም ደግሞ ወጣቶች ቁጭ ብለው በመነጋገር ሀሳብ የሚቀያየሩበትና ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች የጋራ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።

ፕሮጀክቱ ከእንጦጦ ተራራ ተነስቶ ፒያሳን አካሎ እስከ ብሄራዊ ቤተመንግስት የሚዘልቅ እንዲሁም  በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እስከ ብሄራዊ ቤተመንግስት ገራዥ የሚያልፍ ሆኖ እንደማሳያ የሚጀመር ነው ብለዋል።

በከተማዋ የተያዘው የልማት ስትራቴጂ ህዝቦቿ ከልማቱ ጋር የሚያድጉና የሚበለፅጉ እንዲሆኑ የሚያስችል እንጂ አንዱን የህንፃ ባለቤት በማድረግ ሌላውን ለማፈናቀል የሚሰራ አለመሆኑንም ተናግዋል ምክትል ከንቲባው።

የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በበኩላቸው ከተማዋ ብዙ ታላላቅ ቅርሶች ያሏት፣ አብያተ መንግስቶች ፣ ቤተ እምነቶችና  እንደመርካቶ ያሉ የታላላቅ ገበያዎች መገኛ ናት ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ ምርጥ ህዝቦች በፍቅር በአንድነት በደም ተሳስረው የሚኖሩባት ከተማ መሆኗንም አስረድተዋል ኃላፊው።

ራሳችን ተንፍሰንና ተዝናንተን ቁጭ ብለን የምንወያይበት እነጂ የተጣበበ የአስተሳሰብ መንገድ እንዳይኖረን ሰፋ ያለ የስፍራ አጠቃቀምን የሚያሳዩ የቱሪስት መዳረሻዎች የሉንም ያሉት ኃላፊው፤ ፕሮጀክቱ ለልጆቻችን ልናተርፍላቸው የሚገባ የመዝናኛ፣የመነጋገሪያና የመናፈሻ ቦታ እንዳለውም ተናግረዋል።

ከዚህም ባሻገር ልጆቻችን ሌሎች ሰዎችን ጋብዘው የሚጠቀሙበት የቱሪስት መዳረሻ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

ለዚህ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያም የ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም