ሉሲ /ድንቅነሽ/ ወደ መገኛዋ አፋር ክልል ተሸኘች

248

አዲስ አበባ የካቲት 14/2011 የሰው ልጆች የዘር ሀረግ ከአንድ ግንድ የመመዘዙ ማሳያ ሉሲ /ድንቅነሽ/ ወደ መገኛዋ አፋር ክልል ተሸኘች፤ ትውልዱም ጥንታዊውን የኢትዮጵያን ታሪክ በጥላቻና መለያየት ከማጠልሸት እንዲታቀብም መልዕክት ተላለፈ።

"ጉዞ ሉሲ ለሠላምና ለፍቅር" የሽኝት መርሃ ግብር ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሉሲ /ድንቅነሽ/ን ቅሪተ አካል ወደ መገኛዋ አፋር ክልል በመሸኘት በይፋ ተጀምሯል።

መርሃ ግብሩ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ አገራት የሚከወን ሲሆን የፍቅርና የሠላም፣ የመተሳሰብና የአንድነት መልዕክቶች ይተላለፉበታል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ አለመግባባቶችና ግጭቶች የኢትዮጵያዊያንን ታሪክ የማይወክሉ ስለመሆናቸው በአሸኛኘት ስነ ስርዓቱ ላይ ተነግሯል።

አገር ተረካቢው ወጣት የህዝቦችን አንድነት፣ ሠላምና ፍቅር የሚሸረሽሩ ተግባራትን በማውገዝ የድርሻውን እንዲወጣም ተጠይቋል።

ሉሲ ዘር፣ ሃይማኖትና ብሄር ሳትለይ ኢትዮጵያን ከዓለም አገራት ጋር ያስተሳሰረችና የሰው ልጆች መገኛ የመሆኗን አኩሪ ድል ጠብቆ ለማቆየት ጥላቻና መለያየትን ማቆም ይገባል ተብሏል።

በሽኝት ስነ-ስርአቱ ከተሳተፉት ታዳሚያን የሙዚቃ ባለሙያ ዳዊት ይፍሩ እንዳሉት ''ከአንዲት እናት የመጣን ሰዎች አሁን በዚህ ዘመን ላይ መለያየቱ በጣም አሳፋሪ ነው። ሉሲ የሁላችንም እናት ናት ብለን ካመንን እኛ ደግሞ የእሷ ልጆች ከሆንን ልጆች ደግሞ ወንድም እህት አክስት እየተባለ የተራባን ሁላችንም አንድ ዘመዳሞች ሆነን ሳለ ይሄንን የመለያየት መንፈስ መተው አለብን።"

''ወጣቱ ትውልድ በመላ ኢትዮጵያ ምን ላይ ነው ያለነው ለአገራችን ሠላም፣ ለአገራችን ፍቅር፣ ለኢትዮጵያችን ዕድገት፣ ለኢትዮጵያችን አንድነት ምንድነው ልናደርግ የሚገባው ከየት ወዴት ነው እየሄድን ያለነው ስለዚህ ቆም ብለን ማሰብ አለብን” ያለችው  አትሌት ደራርቱ ቱሉ ናት ፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዋና ጸሃፊ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ ኢትዮጵያ አንዱ ሃይማኖት ከሌላው ጋር 'ተቻችሎና ተከባብሮ ለዘመናት የኖረባት አገር ናት' ብለዋል።

መነሻው ያልታወቀ ጥላቻና መለያየት በአገሪቷ ሲያጋጥም አፋጣኝ ምላሽ አለማግኘቱም የዚህ ዋነኛ ማሳያ ነው ሲሉ ነው የተናገሩት።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ሉሲ ኢትዮጵያዊያንን ከሌላው ዓለም ጋር ያቆራኘችና ያስተሳሰረች በመሆኗ 'ከኢትዮጵያም አልፎ ለዓለም ኩራት ናት' ብለዋል።

የሰው ልጆች ሁሉ የዘር ሀረጋቸው ከአንድ ግንድ የሚመዘዝ በመሆኑም የዘረኝነትና የአግላይ አመለካከቶች በታሪክም ይሁን በሃይማኖት ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል።

"ጉዞ ሉሲ ለሠላምና ለፍቅር" መርሃ ግብርን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ከሌሎች ተባባሪ አካላት ጋር በመሆን አዘጋጅቶቷል።

በሳይንሳዊ ስሟ አውስትራሎፒቲከስ አፋራንሲስ በመባል የምትታወቀው ሉሲ ወይም ድንቅነሽ የሰው ልጅን ከየት መጣ የሚለውን ለማወቅ በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተች ቅሪተ አካል ስትሆን 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ እንዳላት ተገምቷል።

ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም በአፋር ክልል አዋሽ ሸለቆ ውስጥ በሚገኝ ሃዳር በተሰኘ አካባቢ የተገኘችው ሉሲ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ ምድር መሆኗን አረጋግጣለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም