በጋምቤላ ጊኒ ዎርምን ለመከላከል ባለሃብቶች ለሰራተኞች የንጹህ መጠጥ ውሃ እንዲያቀርቡ ተጠየቀ

67

ጋምቤላ የካቲት 14/2011 በጋምቤላ ከልል በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች ሰራተኞቻቸውን ከጊኒ ዎርምና ሌሎች ውሃ ወለድ በሽታዎች ለመከላከል ንጹህ የመጠጥ ውሃ የማቅረብ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትርና የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር በአበቦና ጎግ ወረዳዎች ባለሃብቶች ለሰራተኞች በሚያቀርቡት የመጠጥ ውሃ ላይ ውይይትና የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በዚህ ወቅት  እንደተናገሩት መስሪያ ቤታቸው ከውሃና መሰኖ ሚስቴር ጋር በመቀናጀት በገጠር ቀበሌዎች የንጸህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ ለማደረግ በቅንጀት እየሰራ ነው።

በአካባቢው በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለሰራተኞቻቸው ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ማህበረሰብ ጭምር ንፁህ የመጠጥ ውሃ የማቅረብ ማህበራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ከዓመት በፊት በአካባቢው  አንድ ባለሃብት የንፁህ መጠጥ ውሃ ለሰራተኞቹ ባለማቅረቡ ምክንያት 15 ሰራተኞች በጊኒ ዎርም በሽታ ተጠቅተው መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።

ሰራተኞቹን ብሎም የአካባቢውን ማህበረሰብ ከጊኒ ዎርምና ሌሎች ውሃ ወለድ በሽታዎች ለመታደግ ባለሃብቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው መንግስት የንጹህ መጠጠ ውሃ አቅርቦትን በገጠር ቀበሌዎች ተደራሽ በማደረግ ህብረተሰብን ከጊኒ ዎርምና ሌሎች ውሃ ወለድ በሽታዎች ለመጠበቅ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም በክልሉ በግብርና ኢንቨስተመንት የተሰማሩ ባለሃበቶች ለሰራተኞቻቸው የንፁህ የመጠጥ ውሃ የማቅርብ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ባለመቻላቸው ዜጎች ለበሽታዎቹ መጋለጣቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ባለሃብቶች ፍቃድ ሲወስዱ ለሰራተኞቻቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ ለማቅረብ በገቡት ውል መሰረት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳሰበዋል።

በአፍሪካ የአራት ሀገራት የጊኒ ዎርም በሽታ ማጥፊያ ፕሮግራም አምባሳደር የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን በዚሁ ውቅት "ዜጎች ንፁህ የመጠጥ ውሃ የማግኘት ሰባዊ መብት አላቸው "ብለዋል።

በአካባቢው በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩት ባለሃበቶች ግን ለሰራተኞች እያቀረቡት ያለው የመጠጥ ውሃ ለጊኒ ዎርምና ሌሎች የጤና ችግሮች የሚዳርግ መሆኑን በመስክ ምልከታቸው ማረጋገጥ መቻላቸውን ተናግረዋል።

ንጸህ የመጠጥ ውሃ ለሰራተኞች እንዲያቀረቡ አስገዳጅ ሁኔታ ሊቀመጥ እንደሚገባ ዶክተር ጥበበ አስገንዝበዋል።

በመስክ ምልከታው ከተገኙት ባለሃበቶች መካከል የጎይ እርሻ ልማት ስራ አስኪያጅ አቶ ወልዱ መሰለ ከአሁን በፊት ለሰራተኞች የንፁህ መጠጥ ውሃ ማቅረብ ያልተቻለው በአቅም ውስንነት ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

ባለሃብቱ እንዳሉት ድርጅቱ የክልሉን ውሃና መስኖ ሀብት ልማት ቢሮ የቴክኒክ ድጋፍ በመጠየቅ ለሰራተኞች መለስተኛ ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ለማስቆፈር በሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት በሰው ኃይል በማስቆፈር ለሰራተኞቹ የጉድጓድ ውሃ እያቀረደበ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የጎግ ወረዳ ባለሃብት አቶ ሙላት ገብረስለሴ ናቸው።

በቀጣይ ለሰራተኞቹ በማሽን ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ በማስቆፈር ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለማቅረብ የሚያስፈልጉ እቃዎችን በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የጊኒ ዎርም በሽታ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአራት የአፍረካ ሀገራት በስተቀር በሌላው  የዓለም ክፍል መጥፋቱ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም