የአካባቢ ጽዳት የሁሉም ጉዳይ ነው-የኢንቫይሮመንታል ፎረስት ቸሪተብል ሶሳይቲ

154

አዲስአበባ  የካቲት 14/2011 የአካባቢ ጽዳት የሁሉም ጉዳይ በመሆኑ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ።

'የእግር ጉዞ በማድረግና ቆሻሻዎችን በማንሳት ወደ ሃብት እንቀይር /walk and pick trash to cash/በሚል መሪ ሐሳብ መጪው ቅዳሜ ከመስቀል አደባባይ እስከ መገናኛ የጽዳት ዘመቻ ይካሄዳል። 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ስራ እስኪያጅ ዶክተር ተሾመ ቶልቻ እንደገለጹት ተቋማቸው 'ከኢንቫይሮመንታል ፎረስት ቸሪተብል ሶሳይቲ' ከተሰኘ በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር የካቲት 16 ቅዳሜ ከጠዋቱ 2:30 ጀምሮ ከመስቀል አደባባይ እስከ መገናኛ የእግር ጉዞ በማድረግና ቆሻሻዎችን በማንሳት የጽዳት ዘመቻ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ይህ ዘመቻ የሚደረገው በቄርቆስ፣ በቦሌና በየካ ክፍለ ከተማ የጽዳት አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች ጥምረት መሆኑንም ጠቅሰው ተቋሙም የቆሻሻ መጣያ ደስት ቢኖችን በየቦታው ለማስቀመጥና ለማዘምን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዶክተር ተሾመ አያይዘውም ወር በገባ በመጨረሻው ሳምንት ይካሄድ የነበረውና በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር ሃይለማርየም ደሳለኝ ተጀምሮ የነበረው የጽዳት ዘመቻ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን ገልጸው፤ አሁን የሚደረገው ዘመቻ ለተመሳሳይ ስራ መነቃቃትን ሊፈጥር እንደሚችል ተናግረዋል።

የኢንቫይሮመንታል ፎረስት ቻሪተል ሶሳይቲ ድርጅት ተወካይ እና የበጎ ፈቃደኞች አስተባባሪ አቶ ታምሩ ደገፋው  አየር ንብረትን መጠበቅ  እንደ ካንሰርና የአእምሮ በሽታን የመሳሰሉ በሽታዎችን ለመቀነስ እንደሚረዳ ተናግረዋል ።

በቀጣይም በሌሎች ክፍለከተሞችም መሰል ዘመቻ ለማድረግ መታሰቡን ገልጸዋል።

አያይዘውም ሁሉም ህብረተሰብ የኔ ጉዳይ ነው በሚል እሳቤ በጽዳት ዘመቻው አጋርነቱን እንዲያሳይ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም