በአዲስ አበባ የሚገኙ 2 ትላልቅ ወንዞች ዳርቻን ወደ አረንጓዴነት የሚቀይር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

267

አዲስ አበባ የካቲት 14/2011 በአዲስ አበባ የሚገኙ ሁለት ትላልቅ ወንዞች ዳርቻን ወደ ጽዱና አረንጓዴነት የሚቀይር  ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።

ፕሮጀክቱ 56 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚኖረው ሲሆን፤ የአንደኛው ወንዝ ርዝመት 27 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር፣ የሌላኛው ደግሞ  23 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ይሆናል።

በአጠቃላይ በግምት ወደ 29 ቢሊዮን ብር ወጪ ይደረግበታል ተብሏል።

በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ፕሮጀክት ለበርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ተገልጿል።

የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የአዲስ አበባን የነፍስ ወከፍ የአረንጓዴ ሽፋን ከተቀረው የአፍሪካ አካባቢ ጋር ሲነጻጸር ከነበረበት ዜሮ ነጥብ ሦስት ሜትር ኪዩብ ወደ ሰባት ሜትር ኪዩብ ከፍ ያደርገዋል።

https://www.youtube.com/watch?v=2PwOLW0WUUk&t=2s

አረንጓዴና ንጹህ አዲስ አበባን በመፍጠር መዲናዋን  የከተማ ቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ ደግሞ የፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓላማ ነው።

በተለይ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦችን እንዲሁም የእረፍተ ጊዜ ማሳለፊያ ስፈራዎችን በማዘጋጀት የውጪና የአገር ውሰጥ ጎብኚዎችን ለመሳብ እንደሚያስችል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

በወንዞቹ ዳርቻና ሕዝብ በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች የአገልግሎት ዘርፉን በማበረታታት ካፌዎች፣ ምግብ ቤቶች እንዲስፋፉ እድል እንደሚሰጥ ነው የተጠቆመው። ለከተማ አስጎብኚዎች አገልግሎት ማመቻቸት ከውጤቶቹ መካከል ተጠቃሽ ነው።  

ወደ ወንዞቹ የሚቀላቀሉ ፍሳሽ ቆሻሻዎች አቅጣጫቸው ተቀይሮና በዘመናዊ ተክኖሎጂ ታክመው በዳርቻዎቹ የሚተከሉ እጽዋቶችን ለማጠጣት እንደሚውሉም ተገልጿል።

በዝናብ ጊዜ የሚፈጠር ጎርፍ ወደ ወንዞቹ እንዳይገባ በዳርቻዎቹ የማፋሰሻ መስመር እንደሚሰራም ተጠቁሟል።

ፕሮጀክቱ የብስክሌት መስመር፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ  አቅርቦትና የመናፈሻ አገልግሎትን የያዘ ሲሆን፤ በዋናነት ከፀሀይ የሚመነጭ ታዳሽ ሃይልን ይጠቀማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም