ዕምቅ ሀብት ዕምቅ ችግር…

134

በሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ)

ገበያው ብርሃኔ ይባላል። መንግስት የወጪ ንግዱን ለማቀላጠፍ በሚል  በአመቻቸው አሰራረና የብድር ዕድል ተጠቅሞ ሰሊጥና ቦለቄ ወደ ውጭ የመላክ ንግድን ከተቀላቀለ ስድስት አመት አስቆጥሯል። በዚህ በተሰማራበት እና እንጀራው በሆነው የላኪነት ስራ ተግቶ በመስራት ለቤተሰቦቹ የኑሮ መሻሻልን ለሀገሩ ደግሞ የውጪ ምንዛሬን ከማምጣት ባሻገር አገሪቷን ከማስተዋወቅ አንጻርም የራሱን  ሚና ሲጫወት ቆይቷል። በበርካታ መሰናክሎች የተተበተበው  የወጪ ንግድ ስራውን ረጅም ጊዜ በተገቢው ሁኔታ እንዲያከናውን አልፈቀዱለትም።

ለአንድ ሀገር እድገት አስተዋፅኦ ከሚያደርጉ ዘርፎች መካከል የወጪ ንግድ አንዱ መሆኑን በማመን መንግስት ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የንግድ ዘርፉን ለማዘመንና ለማሳደግ  ግብ ነድፎ በመጀመሪያው ዕድገትና ትራንፎርሜሽን ዕቅድ በማካተት መስራት ጀምሮ ነበር። እቅዱ ግን የታሰበውን ያክል ግብ ሊመታ እንዳልቻለ በወቅቱ የተደረገው የዕቅድ ግምገማ ያሳያል።

በመጀመሪያው የእቅድ ዘመን የታዩትን የዘርፉን ማነቆዎች በመለየት የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አንዱ ዋና የትኩረት አቅጣጫ በማድረግ ተይዟል። በዚህ መልኩ ትኩረት መሰጠቱም ለታለመው መዋቅራዊ ሽግግር መሳካት የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማበረታታት የሚደረጉ መጠነ ሰፊ ግንባታዎችና የቴክኖሎጂ ሽግግሮች እንዲሁም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ በየክፍላተ-ኢኮኖሚው የሚደረጉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማምጣት ረገድ የበኩላቸው ሚና እንዲጫዎቱ ታሰቦ ነው፡፡

የኢፌዴሪ ንግድ እና ኢንዱስትር ሚኒስትር የአገሪቱ የወጭ ንግድ ገቢ ዝቅተኛ አፈፃፀም እንደሆነ  እና በ2010 በጀት አመት ከተያዘው 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ውስጥ 1 ነጥብ 21 ብቻ ማስመዝገቡን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የወጪ ንግድ ማስፋፊያ ጀነራል ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡

በተያዘው በጀት አመት በወጭ ንግድ ገቢ ትልቅ ድርሻ ያላቸው እንደ ቡና፣ ጥራጥሬና የቅባት እህሎች አነስተኛ የገቢ አፈፃፀም ሲያስመዘግቡ በአንፃሩ እንደጫት፣ ኤሌክትሪክና ታንታለም ያሉ ምርቶች የተሻለ አፈፃፀም እንዳስመዘገቡም በሪፖርቱ  ተጠቅሷል፡፡

ለአፈፃፀሙ ዝቅተኛ መሆን በአለም ገበያ የምርቶቹ ዋጋ በመውረዱና በአገር ውስጥ የፀጥታ መደፍረስ ችግር በመከሰቱ መሆኑን ኋላፊው አመላክተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት እየታየ ያለውን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ ሂደት የወጪ ንግዱን ለማነቃቃት መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ቢሆንም አፈጻጸሙ ሲታይ ግን አነስተኛ ነው ሲሉም ነው  ሀላፊው የሚገልፁት።  

ለወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት ችግሮች መካከል የመንግስት የአሰራር ቀልጣፋ አለመሆን እና ሸፍጥ ዋናው ማነቆ እንደሆኑ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚሁ ጎን ለጎን የንግድ ሥርዓቱን የሚያዛቡ ሕገ-ወጥ ንግድና የኮንትርባንድ እንቅስቃሴዎች፣ የምርት ጥራት መጓደል ችግሮችና የውጪ ምንዛሬ ግኝትን የሚጐዱ ተግባራት ለዘርፉ ማነቆ ሆነው እንደቆዩ አቶ አሰፋ ጠቅሰዋል።

ሌላው ለወጪ ንግዱ መዳከም አንኳር ብለው ከጠቀሱዋቸው ምክንያቶች ኢትዮጵያ የምትልካቸውን ዋና ዋና ምርቶች ለዓለም ገበያ ማቅረብ ከጀመረች ጊዜ ጀምሮ እሴት ሳይጨመርባቸው የሚላኩ መሆኑ አንዱ ነው፡፡ እሴት ሳይጨመርበት በጥሬው መላኩ እንዳለ ሆኖ፤ የጥራት ጉድለት እያጋጠመው መምጣት ደግሞ ለዘርፉ ሌላው ማነቆ ሆኖ በመቀጠሉ፣ ራሱ በወጪ ንግድ አፈጻጸም ላይ ችግር እየፈጠረ እንደሆነ ከብሄራዊ ባንክና ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ ኢትዮጵያ ኤክስፖርት የምታደርጋቸው ዋና ዋና ምርቶች በአገር ውስጥ ለፍጆታ መዋላቸውና ምርቱን ወደ ገበያ ያለማውጣት ችግርም ለአገሪቱ የወጪ ንግድ መዳከም  ሌላው እንደ ማነቆ የሚታይ ነው፡፡

እንደ አቶ ገበያው ያሉ የተለያዩ ላኪዎች፤ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ላለማደጉ እንደ ዋና ችግር ያቀረቡት ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በመጠንና በጥራት ያለ ማምረት ችግር ነው፡፡ ለወጪ ንግድ የሚሆኑ የግብርና ምርቶችን ምርታማነት ለመጨመር የሚያስችል አሠራር ባለመዘረጋቱ፣ ግብርናው አለመዘመኑና ሰፋፊ እርሻዎች ባለመበረታታቸው የተፈጠረ ችግር እንደሆነ ላኪዎች በየጊዜው የሚያነሱት ሀሳብ ነው፡

ሌላው ዘርፉን እንደ ችንካር ይዞት የቆየው ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ምርት እየተቀየጠና የአንዱ አካባቢ ምርት ከሌላው እየተደባለቀ መቅረቡ ነው። ከየአካባቢው የሚመረተው ምርት በጥራትም በአይነትም ስለሚለያይ እራሱን በየደረጃው ከመላክ ይልቅ በምርት ገበያ አማካኝነት በማሰባሰብ የሚላክበት አሰራር ነው። ይህ ተግባር የውጭ ገዥዎችን እያሸሸ በመሆኑ፣ ከዚህ ቀደም ጥሩ ዋጋ ያስገኝ የነበረው የሐረር ቡና በዚህ ዓይነቱ ተፅዕኖ ስር መውደቁም ነው የሚነገረው።  በእርግጥ በቅርብ ጊዜ አርሶ አደሮች እራሳቸው ያመረቱትን ምርት በቀጥታ መላክ ይችላሉ የሚል ህግ እና አሰራር መዘርጋቱ ለችግሩ እንደ መፍትሄ ይሚወሰድ ተግባር ነው።

ከዚህ ባሻገር የወጪ ንግዱን ወደፊት እንዳይራመድ ካደረጉት ተግባራት መካከል አንዱ በላኪነት ሥራ የሚሰማሩ ነጋዴዎች የብቃት ደረጃ ነው፡፡ የላኪነት ፈቃድ ሲሰጥ የመላክ ፍላጎትን ብቻ ሳይሆን የአቅም ደረጃንና ዝግጁነትን እንዲሁም እውቀትን መሰረት ያደረገ አሰራር መሆን እንዳለበት የተለያዩ ላኪዎች ያስረዳሉ። ከብሄራዊ ባንክ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ዘርፉን በመቀላቀል ለአገሪቷ እሴት እጨምራሉ በሚልና በቤተሰብ የተለያዩ ብድሮች ሲወሰዱ እንደነበር ያሳያል።  አቶ ገበያው ምርት ማሳደግና በጥራት ማቅረብ ላይ ልዩ ትኩረት ተደርጎ መሠራት እንዳለበት ከማመልከታቸውም ባሻገር፣ አምራቾች የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ የመንግሥትና የግል የፋይናንስ ተቋማት ለዚህ አገልግሎት ምቹ እንዲሆኑ መደረግ እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ችግር የነበረባቸው አገሮችን ችግር የፈታው የግል ዘርፉ ነው በማለትም ደቡብ ኮሪያን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡ 

አፍሪካን በንግድ ቀጠና ከማስተሳሰር አንጻር

ንግድ በተለይ የወጪ ንግድ የተለያዩ አገራትን የማስተሳሰርና አንድ ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር ዋነኛ መንገድ ነው። በመሆኑም የአፍሪካ አገራትን ለማገናኘት ያሰበ የአፍሪካ ህብረት በ2063 አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር ነጻ የአፍሪካ ንግድን ለመተግበር  እስከ 34 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የግብርና ምርቶችን ከውጭ የሚያስገቡ በመሆናቸው ሰፊ የገበያ ዕድል መኖሩን ነው፡፡

በአፍሪካ በ54ቱ አገራት ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሕዝብ የሚገኝ ሲሆን፣ የየአገራቱ ጥቅል የኢኮኖሚ አቅም (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) ከ3.4 ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደሚገመት መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ አገራቱ እርስ በርስ ቢገበያዩ፣ ድንበሮቻቸውንና ኬላዎቻቸውን ቢያነሱ፣ በገቢና ወጪ ንግዳቸው ላይ የጣሏቸውን የታሪፍ፣ የኮታ እንዲሁም ሌሎች ታርፍ ነክ ያልሆኑ ከልካይ ሁኔታዎችን እንዲያነሱ ግፊት የሚያደርጉት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና የአፍሪካ ኅብረት አገሮች አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥናታዊ መረጃዎችንና ሌሎችም ማስረጃዎችን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡

የአፍሪካን ነጻ የንግድ ቀጠና ለማስጀመር ባለፈው መስከረም ወር በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ (ኢሲኤ) በተዘጋጀ ውይይት እንደተገለጸው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ለአህጉሪቱ የተለየና ወቅታዊ እድል በመሆኑ ከቀጣናው ውጪ ካሉ የንግድ ስምምነቶች የተሻለ ጥቅም የሚሰጥ መሆኑን በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር ሚስተር አንድሪው ሞልድ ተናግረዋል

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ40 በላይ ለሆኑ ያላደጉ አገሮች የንግድ ዘርፍ ማሳደጊያ ድጋፍ እየሰጠ የሚገኘው የተቀናጀ የንግድ ማሳደጊያ ተቋም፣ በዓለም ንግድ ድርጅት አስተባባሪነት፣ በስድስት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎችና በዓለም የፋይናንስ ተቋማት ተባባሪነት የተመሠረተው ይህ ዓለም አቀፍ የንግድ ማሳደጊያና ማበልጸጊያ ተቋም ዋና ዓላማው፣ ያላደጉ አገሮችን አቅም መገንባት ነው፡፡

ተቋሙ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ የአፍሪካ አገሮችና የመን የታደሙበትን ዓውደ ጥናት በአዲስ አበባ ለሳምንት ያህል ባካሄደበት ወቅት ይፋ ያደረገው ጥናት እንዳመለከተው፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ካለው አቅም በታች፤ ከጠቅላላ አገር ውስጥ ምርት አኳያ ለውጭ ገበያ እያቀረባቸው የሚገኘው የወጪ ንግድ ሸቀጦች ከአሥር በመቶ በታች  ናቸው፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገሮችን የሚወክሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣  ፖሊሲ አውጪዎች፣ የትላልቅ ኩባንያዎች ባለቤቶችና ኃላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ከሚያዝያ 3 እስከ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ጉባኤ እንደሚካሄድ  ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ይህ አይነት ምክክር መደረጉ በአህጉሩ ለተጀመረው የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ዋናኛ መሰረት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። አፍሪካን ያገናኛል ተብሎ የታመነበት እና 44 የአፍሪካ  ሃገራት በዓለማችን ትልቁ ሊባል የሚችለውን ነፃ የንግድ ዝውውር ስምምነት በሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ በፊርማቸው በባለፈው አመት አፅድቀዋል።

በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሥራ ላይ እንደሚውል ተስፋ የተጣለበት ይህ ስምምነት 1.2 ቢሊዮን አፍሪካውያንን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገምቷል።

በመሆኑም ናይጄሪያን ጨምሮ ሌሎች 10 የአፍሪካ ሃገራት ይህን ስምምነት በአፋጣኝ በመፈረም ስምምነቱ እውን እንዲሆንና 54ቱም የአፍሪካ ሃገራት ፊርማቸውን ማሳረፍ እንደሚኖርባቸው ጥሪ ቀርቧል።

በእንግሊዝኛው 'አክፍታ' በሚል ምህፃረ ቃል እየተጠራ ያለው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ዝውውር ስምምነት በአፍሪካ ሃገራት መካከል ድንበር የማያግዳቸው የንግድ ልውውጦች እንዲካሄዱ እንደሚያዝ እየተነገረ ነው።

አልፎም ግብር እና አስመጭዎች ላይ የሚጫነውን ቀረጥ በማስቀረት በአህጉሪቱ ሃገራት መካከል ያለውን ነፃ ዝውውር ያበረታታል ሲሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ጥቅሙን ያስረዳሉ።

የንግድ ቀጠና ማዕቀፉ በዋናነት የአፍሪካ ሃገራትን የእርስ በርስ ንግድ ለማበረታታ ያቀደ ይሁን እንጂ የሥራ ዕድሎች መፍጠርም ትልቁ የስምምነቱ ትሩፋት እንደሚሆን ተገምቷል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የወቅቱ ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ስምምነቱን ''መልካም ፈተና" ሲሉ ቢጠሩትም "የስኬት ጥማት እንዲኖረንና ድፍረት እንድናዳብር ኃይል ይሰጠናል" ብለዋል።

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት እ.ኤ.አ በ2020 የአፍሪካን አገራት የንግድ ልውውጥ በ52 በመቶ እንደሚጨምረው ከአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

በአጠቃላይ በአገራችን ያለውን ዕምቅ ሀብት በመጠቀም የወጪ ንግድ ዘርፉን በማሳደግ የአገሪቷን የውጪ ምንዛሬ ከመጨመሩም በላይ አገሪቷ የምትታወቅበትን አገራዊ ምርቶች ማብዛት የግድ ይላል። ለምሳሌ ሳምሰንግ ሲባል ኮሪያ እንደምንለው ወይም የኖኪያ ስም ሲጠራ ፊንላንድ እንደሚባለው አንድ ነገር መፈጠር አለበት፡፡

የወጪ ንግድ ከሌላው የሚለየው አንድ ቦታ ላይ ያለን ችግር በመቅረፍ ብቻ ውጤት የሚያመጣ ባለመሆኑ፤አሰራሩን ከማዘመን ጀምሮ የላኪዎችን አቅምና ፍላጎት በመጨመር እና ሁሉም ቦታ ያሉትን ችግሮች በመቅረፍ ለዘርፉ ማደግ ሁሉም ሊተባበር ይገባል፡፡

የመሠረተ  ልማት አካባቢ ችግር ካለ የመሠረተ ልማቱን ችግር ብቻ መቅረፍ ትርጉም የለውም፡፡ በጉምሩክ የሚታየውን ችግር በመፍታት ቁጥጥሩን በማጠናከር በህገ ወጥ የሚካሄደውን የወጪ ንግድ ልውውጥ ማስቀረት እንደሚቻል ባለሙያዎች ያስረዳሉ።  ዘርፉን የበለጠ ለማዘመንና የነበሩትን ጥያቄዎች ለመፍታት ከመንግስት ቁርጠኝነት በተጨማሪ የሁሉም ዜጋ ርብርብ ይጠይቃል።  እንደ ሩዋንዳ ያሉ አገሮች እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን አይተው ማስተካከያ በመውሰዳቸው ውጤት አግኝተዋል፡፡ የወጪና ገቢ ንግዳቸውን በተሻለ ፍጥነት ማስተናገድ ችለዋል፡፡

አቶ ገበያው ብርሃኔም በአገሪቷ የመጣውን ለውጥ በመጠቀም ድሮ ሲሰሩ ወደ ነበረው ሥራ ተመልሰው ሰሊጥና ቦለቄ እየላኩ ይገኛሉ። በመሆኑም የብዙ ላኪዎች ችግርና ጥያቄ የነበረውን የምርት ገበያን ረጅም ሂደት በማሳጠር የሚወስደውን ጊዜ ከማሳጠሩም በላይ የምርት መበላሸትን በሚገባ እንደቀነሰላቸው ያስረዳሉ።

ይህን ቀልጣፋ  አሠራር በሚገባ በመጠቀም፤ በዘርፉ ያለውን ብልሹ አሰራርና ሸፍጥ በመፍታት እና ከጎረቤት አገራት ጋር ያለንን ግንኙነት በማጠናከርና እንደ ገበያው ያሉ ላኪዎችን በማበረታታት ብሎም አዳዲስ ላኪዎችን ወደ ዘርፉ በማምጣት አገሪቷ የተየያዘችውን የለውጥ ጉዞ ለማጠናከር መስራት ይገባልና ሁሉም ሊረባረብ ይገባል መልዕክታችን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም