በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ839 ሺህ በላይ ህጻናት የማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍ እና ክብካቤ አገኙ

93

አዳማ የካቲት 14/2011 በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ839 ሺህ በላይ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህጻናት የማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍ እና ክብካቤ ማግኘታቸውን የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። 

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስትራተጂካዊ ሥራ አመራር ዳይሬክቶሬት ተወካይ ዳይሬክተር አቶ በሽር ሳልህ ለኢዜአ እንደገለጹት ህጻናቱ ድጋፍ እና ክብካቤ ያገኙት ባለፉት ስድስት ወራት ነው።

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ህጻናት ማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማድረግ በተሰራው ሥራም አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።

ባለፉት ስድስት ወራት 839 ሺህ 889 ለችግር የተጋለጡ ህፃናት በተለያዩ የድጋፍ ስልቶች መታቀፋቸውን ጠቁመው በእዚህም ከቤተሰብ ጋር መልሶ ማቀላቀል፣ ከጎዳና ማንሳትና የትምህርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

አቶ በሽር እንዳሉት ማህበረሰብ አቀፍ የህፃናት ድጋፍና ክብካቤ ፕሮጀክትን በመቅረጽና ከ311 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከማህበረሰቡ በማሰባሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል።

በተጨማሪም 2 ሺህ 626 ለችግር የተጋለጡ ታዳጊ ህጻናት የሥራ ዕድል እንዲመቻችላቸው ከክልልና ከፌደራል የሥራ ዕድል ፈጠራ ኤጀንሲ ጋር የማስተሳሰር ሥራ ተከናውኗል።

የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናቶች ሁለገብ የማህበራዊ ቁጠባ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉንም ነው ያመለከቱት።

በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 3 ሺህ 732 ህጻናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ መደረጉን የገለጹት ደግሞ በኦሮሚያ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የህፃናት ቤተሰብ ማፈላለግና ማቀላቀል ከፍተኛ ባለሙያ አቶ እውነቱ ቡሼ ናቸው።

ህፃናቱ በዋናነትበትዳር መፍራስ፣ በኤች አይ ቪ/ኤድስና ተዛማጅ በሽታዎች ወላጆቻቸውን በማጣት፣ በቤተሰብ መካከል በተፈጠሩ አለመግባባቶችና በድህነት ምክንያት ለአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ መጋለጣቸውን ጠቁመዋል።

እንደባለሙያው ገለጻ በአብዛኛው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ልጆች ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች ሲሆኑ የትምህርት ደረጃቸውም ከ8ኛ ክፍል በታች መሆኑን በክልሉ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ተረጋግጧል።

ህጻናቱን ከጎዳና ከማንሳት ባለፈ የስነልቦናና የምክር አገልግሎት ፍላጎታቸውን በመለየት የስነ ምግባር ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል።

መማር ለሚፈልጉት ህጻናትም  ቤተሰቦቻቸው ባሉበት አካባቢ የትምህርት እድል እንዲመቻችላቸውና መስራት ለሚችሉት ደግሞ የሥራ እድል ለመፍጠር ጭምር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ3 ሚሊዮን በላይ ህጻናት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙና ልዩ ድጋፍና እንክብካቤ የሚሹ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ዑቦንግ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት የማህብረሰብ አቀፍ የህፃናት ድጋፍና እንክብካቤ ሥራን አጠናክሮ ለማስቀጠል የህዝቡን ግንዛቤ ከመለወጥ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም