ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ መርካታቸውን በባሌ ሮቤ አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ

79
ጎባ ሚያዝያ 27/2010 ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ጋር በነበራቸው ውይይት ላነሷቸው ጥያቄዎች በተሰጡ ምላሾችና ማብራሪያ መርካታቸውን በውይይቱ የተሳተፉ አባ ገዳና ሌሎች የሕብረተሰብ ተወካዮች ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በባሌ ሮቤ አባ ገዳ አዳራሽ  ከዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ከመጡ የሕብረተሰብ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል። በመድረኩም ምላሽ ይፈልጋሉ በተባሉ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል። መንገድን ጨምሮ የመሰረት ልማት ጥያቄዎች አለመመለስ ፣ የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራሮች መንሰራፋት፣ በከፍተኛ አመራር ደረጃ የተደረገው የጥልቅ ተሃድሶ እስከ ታች የአስተዳደር እርከን አለመውረድ ፤ የሙስናና  የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር  ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል ይጠቀሳሉ። በውይይቱ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል አባ ገዳ ሀጂ አሎ ኡሰማን  በለይ ለኢዜአ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝቡ በስፋት ለነሳው የመልካም አስተዳደር ችግር መንግስት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጠንክሮ ይሰራል ማለታቸው  ለችግሩ እልባት ማግኘት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገ ውይይት ላነሷቸው ጥያቄዎች በቂ ምላሽና ማብራሪያ በማግኘታቸው መርካታቸውን የተናገሩት ደግሞ የሀገር ሽማግሌው አቶ ሀሰን ከድር ናቸው ፡፡ የህዝቡን ተጠቃሚነት እንዳይረጋገጥ ማነቆ እየሆኑ የሚገኙ የኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሰራሮችን መንግስት ያለርህራሄ ይታገለል ማለታቸው ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሌላው የሀገር ሽማግሌ ሼክ ቃሲም ሁሴን በበኩላቸው "ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚያደርጉት ውይይት በሀገሪቱ ሰላምና ቀጣይነት ያለው እድገት እንዲረጋገጥ ትልቅ ድርሻ አለው "ብለዋል፡፡ በቀጣይነትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሀገሪቱ ለውጥ ህዝቡ ከጎኔ መቆም  አለበት ላሉት ጥሪ የበኩላቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተሳታፊዎች  በሰጡት ምላሽ " መንግስት ህዝቡ የሚያነሳውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በቁርጠኝነት ይሰራል "ብለዋል፡፡ መንግስት ህዝቡን በሚያማርሩ ኪራይ ሰብሳቢ አመራሮች ላይ ያለርህራሄ እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቀዋል፡፡ ህዝቡ ከጥልቅ ተሃድሶ ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ በቀጣይነትም ከህዝቡ ጋር በመሆን ሁሉንም የመንግስት መዋቅሮች በድጋሚ እንደሚፈተሹ ለህዝቡ አረጋግጧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት በሀገሪቱ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት በሚደርገው ጥረት ህዝቡ ከጎኑ እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም