የወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ቡድን ራሱን እንዲያሻሽል ደጋፊዎች ጠየቁ

73

ሶዶ የካቲት 14/2011 የወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ቡድን በሁለተኛው አጋማሽ የውድድር ዘመን ራሱን አሻሽሎ እንዲቀርብ የደጋፊ ማህበር ጠየቀ፡፡

ክለቡ በበኩሉ በመጀመሪያው አጋማሽ የውድድር ዘመን እንዲዳከም ያደረጉ ችግሮችን በመለየት ከገባበት የውጤት ቀውስ ወጥቶ ውጤታማና ተፎካካሪ ለመሆን እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በወላይታ ሶዶ ዞኑ የኪንዶ ኮይሻ ወረዳ ደጋፊዎች አስተባባሪ ወይዘሮ እታገኘሁ ኦርጂሎ እንዳሉት የወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ቡድን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመስርቶ ውጤታማ የሆነው ህዝባዊ መሰረቱ ጠንካራ በመሆኑ ነው፡፡

ክለቡ ባለፈው ዓመት እስከ ግብጽ ድረስ ሄዶ ባደረገው ጠንካራ ፉክክር የነበረውን ሁኔታ አስታውሰው “በዘንድሮ ዓመት ከታሰበው በታች ዝቅተኛ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑ ደጋፊውን አስከፍቷል” ብለዋል

እንደአስተባባሪዋ ገለጻ ከአቅም በታች መጫወት፣ ትኩረት ማነስ እንዲሁም የተጨዋቾች ስነ-ምግባር ጉድለት በቡድኑ ላይ ከሚስተዋሉ ችግሮች ዋንኞች ሲሆኑ በእዚህም የተመዘገበው አነስተኛ ውጤት የደጋፊውን ስሜት እየጎዱ በመሆኑ ክለቡ ለቀጣይ ሁለተኛው አጋማሽ ውድድር ራሱን እንዲያሻሽል ጠይቀዋል፡፡

“አካባቢውን የሚወክል ቡድን መኖሩ ከመዝናኛነት ባሻገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው ” ያሉት ደግሞ ከሁምቦ ወረዳ የቡድኑ ደጋፊዎች ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ አባል አቶ ተስፋዬ አዴ ናቸው፡፡

በቡድኑ ውስጥ እየተስተዋለ ያለው የመልካም አስተዳደር ዕጥረትና የአሰራር ክፍተት የወለደው የእርስ በርስ መከፋፈልና የቡድን መንፈስ ማጣት ቡድኑ ለገጠመው የውጤት ቀውስ ምክንያቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

"ከአቅም በታች የሚጫወቱና ተጎዳሁ በሚል ሰበብ ዝም ብሎ ደመወዝ የሚከፈላቸውን መቆጣጠር ይገባል” ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ ቡድኑ በተለያዩ ጥቅሞች በመተሳሰር አቅም የሌላቸውን ተጫዋቾች ከማዛወርና አቅፎ ከማስቀመጥ መቆጠብ እንዳለበት ገልጸዋል።

የወላይታ ዲቻ ስፖርት ክለብ የደጋፊዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አንዱዓለም ሽብሩ በበኩላቸው ክለቡ ደጋፊውና ህዝቡ በሚፈልገው ልክ ውጤታማ እየሆነ አለመምጣቱ ቅሬታዎችን እያስነሳ መሆኑን ገልጸዋል።

“የመልካም አስተዳደርና መሰል ችግሮች በቡድኑ ውስጥ የአንድነት መንፈስና መነሳሳትን በማሳጣት ቡድኑ የውጤት ቀውስ ውስጥ እንዲገባ አድርገዋል" ብለዋል።

ቡድኑ በህዝቡ ድጋፍ የተቋቋመ በመሆኑ የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት መስራት እንዳለበት ጠቁመው ቡድኑ እየተፈታተነው ያለውን ስፖርታዊ ጨዋነት ማስተካከል እንዳለበት ገልጸዋል።

ችግሩን ጊዜ ሳይወስድ ለመፍታት በአመራሮችና ተጨዋቾች ላይ ቦርዱ ተገቢ የሆነ እርምት እርምጃ ቢወስድም በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የወላይታ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪና የክለቡ ቦርድ ፕረዚዳንት አቶ ፍሬው ሞገስ በበኩላቸው ከደጋፊዎች እየተነሱ ያሉ ቅሬታዎች ትክክል መሆናቸውንና ለክለቡ የውጤት መውደቅ ምክንያት የሆኑት ተለይተው ተገቢ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዚህ መነሻም የቡድኑን ዋና አሰልጣኝ በስምምነት ከማሰናበት ባለፈ ለሥራ አስኬያጅ፣ ለቴክኒካል ዳይሬክተርና ለቡድን መሪው እስከሚቀጥሉት ሁለት ጨዋታዎች ድረስ ያለውን መሻሻል ለማየት ብቻ በሚቆይ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን አስረድተዋል፡፡

ከአቅም በታች መጫወት፣ ከፍተኛ የሆነ የዲሲፕሊን ችግር በመፍጠር ለቡድን መንፈስ መናጋት ምክንያት የሆኑ ተጨዋቾችን በማጣራት አንዱን በማሰናበት ለሦስት ተጨዋቾች ደግሞ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱንም አስረድተዋል።

“የዋና አሰልጣኝ ቅጥርና የተጨዋቾች ግዥ በተመለከተ የሚነሱ ችግሮችን በማስወገድ በግልጽ ማስታወቂያና በቂ መስፈርት በማዘጋጀት ይከናወናል” ብለዋል፡፡

ከእዚህ በተጨማሪ ቡድኑ ካለበት የውጤት ቀውስ መውጣት ብቻ ሳይሆን የሚታወቅበትን የተፎካካሪነትና የቡድን ስሜት ለመመለስ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም