በባሌ ዞን በገጠር መንገድና ድልድይ ሥራ ለተሰማሩ ወጣቶች የ20 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር ተፈጠረ

80

ጎባ የካቲት 13/2011 በባሌ ዞን በማህበር ተደራጅተው በገጠር መንገድና ድልድይ ሥራ ለተሰማሩ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ሙሩቃን የ20 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር መፈጠሩን የዞኑ መንገዶች ባለስልጣን ገለጸ፡፡ 

በገጠር መንገድናየድልድይ ግንባታ ሥራ በመሰማራታቸው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከመሆናቸው ባሻገር ልምድ ካላቸው ተቋራጮች እውቀት ለመቅሰም መቻላቸውን በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ገለጹ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ገዛኽኝ ደጀኔ ለኢዜአ እንዳሉት የገበያ ትስስር የተፈጠረው በምህንድስናና ተያያዥ የሙያ ዘርፎች ተመርቀው በመንገድና በድልድይ ግንባታ የሥራ ዘርፍ ለተደራጁ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሙሩቃን ነው፡፡

በዚህም በዘጠኝ ማህበራት ስር ለተደራጁ ወጣቶች ከ20 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ የገበያ ትስስር መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት ማህበራቱ የገጠር መንገድን ከሚገነቡ ዋና ተቋራጮች ጋር በመቀናጀት በዞኑ ስድስት ወረዳዎች ውስጥ ዘጠኝ ድልድዮችን በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡

ወጣቶቹ በመንገድ ግንባታ ሥራም ተሰማርተው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከመሆናቸው ባለፈ ልምድ ካላቸው ተቋራጮች እውቀት እየገበዩ መሆናቸውን ኃላፊው አቶ ገዛኽኝ ተናግረዋል፡፡

እንደእርሳቸው ገለጻ በዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት የድልድዮች ግንባታን ጨምሮ ከ330 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የ206 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ግንባታ ሥራ እየተከናወና ይገኛል።

"እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴም የሦስት ድልድዮችና የ156 ኪሎ ሜትር የመንገድ ሥራ ተጠናቋል" ብለዋል፡፡

የዞኑ የሥራ እድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጫልችሳ ዘውዴ በበኩላቸው በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት በመንገድ ግንባታ ዘርፍ የገበያ ትስስር የተፈጠራላቸውን ጨምሮ 11 ሺህ 800 የሚሆኑ ወጣቶች የገበያ ትስስር ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በገበያ ትስስሩም በገጠርና ከተማ በተለያዩ ኢንተርፕራይዞች ስር የተደራጁ ወጣቶች ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የገበያ ትስስር የተፈጠረው ኢንተርፕራይዞችን ከመንግስት ፕሮጀክቶች፣ ከግል ባለሀብቶች፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ከማራሚያ ቤቶችና ሌሎች ተቋማት ጋር በማቀናጀት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት በዞኑ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ከ451 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡

በዞኑ ደሎ መና ወረዳ የደዩ ድልድይ በመገንባት ላይ የሚገኙት ወጣቶች ተወካይ ከዲር ማህሙድ እንደገለፀው በ2010 ዓ.ም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምህንድስና ተያያዥ ሙያዎች ከተመረቁ ሌሎች አምስት ጓደኞቹ ጋር መደራጀቱን ተናግሯል።

በተያዘው ዓመት “ደዩ” ላይ እየተገነባ ለሚገኘው ድልድይ ከመንገዶች ባለስልጣን የ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የኮንትራት ውል ተፈራርመው ስራውን በማከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡

" የድልድዩን ግንባታ ሥራ በሚፈለገው የጥራት ደረጃ ገንብቶ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት በቁርጠኝነት እየሰራን ነው" ብሏል ።

በገጠር መንገድና ድልድይ ግንባታ ሥራ መሰማራታቸው ከራሳቸው ባለፈ ለሌሎች አስር ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንዳስቻላቸው የተናገረው ደግሞ በበርበሬ ወረዳ በመንገድ ግንባታ ዘርፍ የተሰማራው "አል-አሪፍ ፍሮምሳና ጓደኞቹ ማህበር" ተወካይ አሪፍ አህመድ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅትም በበርበሬ ወረዳ “ሀምበላ” በተባለ አካባቢ እየገነቡት ላለው ዘመናዊ ድልድይ የ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የኮንትራት ውል ተፈራርመውና ቅድመ ክፍያ ወስደው የግንባታ ሥራውን እያቀላጠፉ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡

በባሌ ዞን በድልድዮቹና በመንገዶቹ ግንባታ ሥራዎች ከሚሳተፉት አካላት መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃንና በመንገድ ዘርፍ የተደራጁ ወጣቶች እንዲሆኑ ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑን ከዞኑ መንገዶች ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም