ዓለም አቀፍ የአፍ መፍቻ ቋንቋና የመናገር ቀን በዓል በአሰላ ከተማ እየተከበረ ነው

144

አዳማ የካቲት 13/2011 የአለም አቀፉ የቋንቋ ቀን መከበሩ ቋንቋዎች እንዳይጠፋ ጥበቃ ለማድረግና ለማበልጸግ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ20ኛ በሀገራችን ደግሞ ለዘጠነኛ ጊዜ በአፍ መፍቻ ቋንቋና  የመናገር ቀን በዓል በአሰላ ከተማ እየተከበረ ነው።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መሐመድ አህመድን በዚህ ወቅት እንዳሉት የአለም አቀፍ የቋንቋ ቀን መከበሩ ቋንቋዎች እንዳይጠፋ፣እንዲያድጉና እንዲበለጽጉ ይረዳል።

" ቋንቋ የመማር፣ የእውቀትና የልማት ምንጭ ነው " ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው እስካሁን በተደረጉ የቋንቋ ልማት እንቅስቃሴዎች በኢትዮጵያ  53 ቋንቋዎች የትምህርት ስርዓት ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን አመልክተዋል፡፡

ከነዚህም  12 ቋንቋዎች በሳባና 44 በላቲን ፊደል የሚጠቀሙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት 27 ቋንቋዎች በ10ኛ ክፍል ደረጃ ብሄራዊ ፈተና እየተሰጠባቸው ሲሆን ዘጠኝ ቋንቋዎች ደግሞ በዩኒቨርስቲ ውስጥ በድግሪ ደረጃ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ስልጠና እየተሰጣባቸው ይገኛል፡፡

በተለይ ሕፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር የትምህርት ተሳትፎን እንዲያድግና  ጥራቱንም በሚፈለገው ደረጃ እንዲደርስ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋና የጋራ ባህል ልማት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ጌታቸው በበኩላቸው "በዓሉ የሚከበረው " አገርኛ ቋንቋዎች ለልማት፣ለሰላም ግንባታና ለአብሮነታችን"  በሚል ዓለም አቀፋዊ መርህ መሆኑን ተናግረዋል።

የበዓሉ መከበር የህዝብ ለህዝብ ትስስርና በባህል መካከል የሚኖረውን መስተጋብርን እንደሚያጠናክርም አብራርተዋል፡፡

ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች  በሚከበረው በዓሉ ከኦሮሚያ ትምህርት ቢሮና ከሌሎችም አካላት በተጋበዙ ምሁሯን የአፍ መፍቻ ቋንቋን በተመለከተ ጥናታዊ ጹሁፍ ቀርቦ ውይይት  እንደሚደረግበት  ይጠበቃል።

በዓሉ የትምህርት ሚኒስቴር ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ከኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ነው የተዘጋጀው።

ባንግላዴሽ ፓክሲታን ግዛት ስር በነበረችበት ወቅት የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው "ባንግሎር " እውቅና እንዲሰጠው ጥያቄ ያነሱት አራት ተማሪዎች ህይወታቸው እንዲጠፋ መደረጉ ተወስቷል

በዚህም ምክንያት ዕለቱን ለማስተዋስ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፥ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም /ዩኔስኮ/ አጠቃላይ ጉባኤ  በየዓመቱ የአፍ መፍቻ ቋንቋ እንዲከበር መወሰኑ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም