የተመጣጠነ የከተሞች እድገት በማረጋገጥ ጫናዎችና ችግሮችን መፍታት ይገባል – የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን

619

አዲስ አበባ የካቲት 13/2011 የተመጣጠነ የከተሞች እድገት በማረጋገጥ ጫናዎችና ችግሮችን ማስወገድ እንደሚገባ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት በሚተገበረው ‘የከተማ ልማትና ቤቶች ዘርፍ የ15 ዓመት ረቂቅ መሪ የልማት እቅድ’ ላይ በከተሞች ፎረም ከተገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።

ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በኢትዮጵያ የሚገኙ ከተሞች በአንደኛ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ የተከፋፈሉ ቢሆኑም የእድገት መጠናቸው ተመሳሳይ አለመሆኑን ተናግረዋል።

የከተሞች እድገትና የህዝብ አሰፋፈር የተበታተነና ወጥ አለመሆን እንዲሁም ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሱ ወጣቶች ቁጥር በዋና ዋና ከተሞች ላይ ጫናና መጨናነቅ እየፈጠረ ነው።

በመሆኑም በአገሪቱ ከ2013 ዓ.ምጀምሮ ለመተግበር እየተዘጋጀ ያለው ዘላቂ የእድገት መሪ ፕላን በከተሞች መካከል የተመጣጠነ እድገት መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ዘላቂ የእድገት መሪ ፕላኑ በከተሞች መካከል ያለውን ጤናማ ያልሆነ ልዩነት ለማጥበብ እንደሚያስችልም ጠቅሰዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው የ10 ዓመቱ ዘላቂ የእድገት መሪ ፕላን በከተሞች መካከል የተመጣጠነ እድገት እንዲኖርና ፖሊሲዎችና መመሪያዎችን ወጥ በሆነ መልኩ መተግበር ያስችላል ነው ያሉት።

መሪ ፕላኑ በደረጃ የተከፋፈሉትን ከተሞች በምን ዓይነት ፕላን፣ የቤት አቅርቦት፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታና መሰል ዘርፎች የተመጣጠነ እድገት እንደሚፈጠር በግልጽ በማብራራቱ አተገባበሩ ቀላልና ውጤታማ እንዲሆን እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ለዚህም የመሬት አቅርቦትን ማሻሻል፣ ህገ ወጥነትን መከላከል፣ የግሉን ዘርፍ በስፋት ማሳተፍና የከተሞችን ገቢ ማሳደግ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

ይህም በከተሞች መስፋፋትና ልማት አማካኝነት የሚፈጠረውን ማህበራዊና አካባቢያዊ ችግሮች ማቃለል እንደሚያስችል አክለዋል።

የረቂቅ መሪ ፕላኑ አቅራቢዎች እንደገለጹት ፕላኑን የ15 ዓመት ለማድረግ እየተሰራ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ ከፈረመችው የተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች ጋር ለማስተሳሳር ሲባል 10 ዓመት እንዲሆን ተደርጓል።

መሪ ፕላኑ የከተሞች እድገትና ትስስር ጉዳዮችን አተገባበር በዝርዝር እንደሚያስቀምጥ ገልጸው ይህም በከተሞች መካከል የተመጣጠነ እድገት እንዲኖርና ከተሞችም የሚጠበቁባቸውን ተግባራት እንዲያውቁ እንደሚያስችላቸው አብራርተዋል።

የረቂቅ መሪ ፕላኑ አቅራቢ ዶክተር በሪሁን አሰፋ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት የከተሜነትና ከተማ መስፋፋት እንደሚፈጠር ጠቁመው ይህን ለመቋቋም መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

በመኖሪያ ቤት ተደራሽነት፣ በፋይናንስ አቅርቦት፣ ተቋማዊና አስተዳደራዊ ተግዳሮቶችን በህግ ማዕቀፍ በመፍታት፣ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ፣ ወጤታማ የመሬት አጠቃቀም በመዘርጋትና ከተሞች የራሳቸውን ገቢ በብድር ጭምር እንዲያገኙ ማድረግ ከመንግስትና ከባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ነው ሲሉ ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።

ሌላው አቅራቢ ዶክተር ፍሬው በቀለም መንግስት ከከተሜነትና ከተማ መስፋፋት ጋር ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለማስወገድ በ2ኛ ደረጃ የሚኙ ከተሞችን መደገፍ፣ የተበታተኑ የህዝብ አሰፋፈሮችን ማስተካከል፣ ፍልሰትና የስራ ቅጥር ሁኔታን መከታተልና መቆጣጠር በትኩረት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።