የተጣለው ትጥቅ ይዞ የመንቀሳቀስ ክልከላ የአካባቢውን ሰላም ወደነበረበት ይመልሳል...የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች

75

ጎንደር የካቲት 13/2011 በማዕካላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት ተከትሎ የተጣለው ትጥቅ ይዞ የመንቀሳቀስ ክልከላ የአካባቢውን ሰላም ወደ ነበረበት ይመልሳል የሚል እምነት እንዳሳደረባቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ 

ከነዋሪዎች መካከል አቶ ሃብታሙ አማረ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት በአካባቢው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንና የሀገር መከላከያ ሠራዊት በጥምረት ያስቀመጡት ክልከላ ተገቢ ነው፡፡

በጎንደር ከተማና አካባቢዋ በሚስተዋሉ አለመረጋጋቶች የንግድ ሥራቸውን በተገቢው መንገድ ለማከናውን መቸገራቸውንና ሁሌም ስጋት እንደሚሰማቸው ገልፀዋል፡፡

" በከተማዋ የጦር መሳሪያ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣት አንድ ቀን ችግር ይፈጠር ይሆን " የሚል ስጋት ውስጥ ከቷቸው የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ክልከላው መደረጉ ከስጋት እንዳዳናቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ ሀብታሙ እንዳሉት ክልከላው የአካባቢውን ሰላም ለመመለስ ጠቀሜታ ስላለው መንግስት ለአካባቢው ዘለቄታዊ መፍትሔ መስጠት የሚያስችሉ ተጨማሪ ስራዎችን መስራት ይኖርበታል፡፡

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት አዝመራው እሸቴ በበኩሉ ከጎንደር መተማ ለህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጡ ተሸከርካሪዎች ላይ የተመሰረተ ገቢ አንደነበረው አስታውሶ፣ በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት ለአራት ወር ያክል ሥራ በመፍታቱ ለችግር መዳረጉን ተናግሯል፡፡

ሰው በየመንገዱ ታፍኖ በታጣቂዎች እየተወሰደ ገንዘብ የሚጠየቅበት ሁኔታ ተከስቶ እንደነበር የገለጸው ወጣቱ ይህም በነጻነት ለመንቀሳቀስ ችግር ፈጥሮ እንደነበር ተናግሯል።

"እስካሁን ሥራፈትቼ በቆየሁበት ጊዜ የቆጠብኩትን ገንዘብ አውጥቼ ስጠቀም ቆይቺያለሁ" ያለው ወጣት አዝመራው፣ በአሁኑ ወቅት በተጣለው ክልከላ መሰረት የፀጥታ ችግሩ ተፈቶ ወደ ሥራው ለመመለስ ተስፋ ማድረጉን ተናግሯል፡፡

" ጎንደር የቱሪዝም መዳረሻና ከፍተኛ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግባት ከተማ በመሆኗ ሰላሟን መጠበቅ ከመንግስት ይጠበቃል" ያሉት ደግሞ አቶ ውብሸት አዳነ የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡

ህዝቡም ከተከለከሉ ተግባራት በመታቀብና አጥፊዎችን ለፀጥታ አካላት አሳልፎ በመስጠት መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ መደገፍ እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

"ቀደም ሲል በነበሩ ቀናት ከምሽቱ 12፡00 በኋላ የህዝቡ እንቅስቃሴ የተገታ ነበር" ያሉት አቶ ውብሸት ትጥቅ ይዞ መንቀሳቀስ ከተከለከለ በኋላ በነጻነት የመንቀሳቀስ ሁኔታ ማሻሻሉን ጠቁመዋል፡፡

ክልከላው የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ከሚኖረው ፋይዳ በተጨማሪ ከቄያቸው ለተፈናቀሉና እርዳታ ለሚሹ ወገኖች የሚያስፈልገውን እርዳታ ለማድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡

"በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረ የጸጥታ ስጋት በሪፈር የተላከች ነፍሰጡር እናት ወደ ጎንደር ከተማ መጥታ የማትገላገልበት፣ ህዝቡ ላላስፈላጊ ወጭና እንግልት የተዳረገበት እንዲሁም በከንቱ የሰዎች ህይወት ይጠፋ የነበረበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሸጋ አድምጠው የተባሉ ነዋሪ ናቸው።

እርሳቸው እንዳሉት ከጎንደር መተማ ለትራንስፖርት ይከፍሉ የነበረው 75 ብር በአሁኑ ወቅት 200 ብር እየተጠየቁ ነው፤ ባስ ሲል ደግሞ በአብርሃጅራ በኩል እስከ 500 ብር ድረስ በመክፈል ለብዝበዛ እየተዳረጉ ነው።

በመሆኑም መንግስት ይህን ችግር ተረድቶ ወደ ህጋዊ እርምጃ መግባቱ አካባቢው ሰላማዊ ሆኖ ይህ ችግራቸው እንዲፈታ የሚያደርግ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

አካባቢው የልማት ቀጠና በመሆኑና የሀገሪቱ የገቢና ወጭ ንግድ ከሚተላለፍባቸው መንገዶች አንዱ በመሆኑ ሰላምን ለማስጠበቅ በመንግስት በኩል የተደረገው ክልከላ እንደሚደግፉትም ተናግረዋል።

የመከላከያ ሰራዊት 33ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥና የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር  በጎንደርና አካባቢው ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ላይ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ክልከላው ካለፈው እሁድ ጀምሮ በጊዜያዊነት መቀመጡ ይታወሳል።

በእዚህም ሰላሙ ወደ ነበረበት እስኪመለስ ድረስ ከጎንደር መተማ እና ከጎንደር ሁመራ በሚወስደው መንገድ ግራና ቀኝ በ5 ኪሎ ሜትር ርቀት በቡድንም ሆነ በተናጥል ትጥቅ ይዞ የመንቀሳቀስ ክልከላ መጣሉ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም