ሃዋሳ ነገ ለምታስተናግደው ሰልፍ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የከተማው ፖሊስ ገለጸ

143


ሀዋሳ የካቲት 13/2011 በሃዋሳ ከተማ ነገ ለሚካሄደው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ይፋጠንልን ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የሃዋሳ ከተማ ፖሊስ አስታወቀ።

የከተማው ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር መስፍን ዴቢሶ ለኢዜአ እንደገለጹት ነገ በሃዋሳ የሚካሄደውን ሰልፍ ተከትሎ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ተደርጓል።

የከተማው ፖሊስ ከዞን፣ ከክልሉ ልዩ ሃይልና ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ሰልፉ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች በቂ ጥበቃ ያደርጋልም ብለዋል፡፡

ፖሊስ አዛዡ እንዳሉት ከሪፈራል አደባባይ ጠዋት አንድ ሰዓት የሚጀመረው ሰላማዊ ሰልፍ መዳረሻው ከቀኑ ስድስት ሰዓት ሃዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም ነው፡፡

ሰልፉ ወደ ብሉናይል የሚያወጣውን አስፓልት ይዞ ተስፋዬ ግዛው ህንጻ አደባባይ ሲደርስ ወደ ሃዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም እንደሚገባና ማጠቃለያውን እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ምክንያት መንገዶቹ ለተሸከርካሪ ዝግ ይሆናሉ ያሉት ኮማንደር መስፍን፤ በበቂ የፀጥታ ሃይል ጥበቃ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡

የከተማው ነዋሪ በሰልፉ ምክንያት ስጋት ውስጥ እንዳይገባ በየክፍለ ከተማው ውይይት መደረጉን ገልጸው ህዝቡም ለሰልፉ ሰላማዊነት የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ የሚዲያ ተጠሪ አቶ ሳሙኤል በላይነህ በበኩሉ የሲዳማ ብሄር በክልል የመደራጀት ህገ-መንግስታዊ ጥያቄውን ተከትሎ ህዝበ ውሳኔው በመዘግየቱ የተዘጋጀ ሰልፍ ነው” ብለሏል።

ዓላማውም “ከዞን ምክር ቤት ጀምሮ በክልሉ ምክር ቤት ጸድቆ ለህዝበ ውሳኔ ለምርጫ ቦርድ የተላከው ሪፈረንደም ጥያቄ ዘግይቷል ይፋጠንልን” የሚል መሆኑን ተናግሯል።

ጥያቄው ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ተከትሎ የቀረበ ቢሆንም ምላሹ በመዘግየቱ በዞኑ ካሉ ወረዳዎችና ከሃዋሳ ከተማ የተውጣጡ ነዋሪዎች መንግስትን በሰላማዊ መንገድ የሚጠይቁበት እንደሆነም ተናግሯል፡፡

“ሰልፉ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ከከተማው ፖሊስና ከሃዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው” ብሏል፡፡

በሰላማዊ ሰልፉ የመንግስት አካላት፣የተለያዩ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የሰልፉ ደጋፊዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም