በብሔራዊ ፓርኮች ላይ እየደረሰ ያለውን ውድመት ለመታደግ እየተሰራ ነው

85

ባህር ዳር  የካቲት 13/2011 በኢትዮጵያ የሚገኙ 27 ብሔራዊ ፓርኮች እየደረሰባቸው ካለው የብዝሃ ህይወት ውድመት ለመታደግ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ  ለኢዜአ እንዳስታወቁት በፓርኮቹ እየደረሰ ያለው ውድመት ፓርኮቹ  አደጋ ላይ እንዲወድቁ እያደረገ ነው።

በአሁኑ ወቅት ለአደጋ ከተጋለጡት ፓርኮች መካከልም የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ አልጣሽ ብሐራዊ ፓርክ፣ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

በፓርኮቹ ዙሪያ የሚኖረው ህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የእርሻ መሬት መስፋፋት፣ የደን ምንጣሮ፣ የእሳት ቃጠሎ፣ ልቅ ግጦሽና መሰል ችግሮች መስፋፋት ለፓርኮቹ አደጋ ሆኗል፡፡

" በየደረጃው የሚገኘው አመራር፣ በህብረተሰቡና በባለድርሻ አካላት ላይ የሚስተዋለው የግንዛቤና የአመለካከት ክፍተት የጎላ መሆኑ ችግሩ እንዲባባስ አድርጓል " ሲሉም አቶ ኩመራ ገልጸዋል፡፡

ፓርኮቹን ከውድመት ለመታደግም ባለስልጣኑ አዳዲስ አሰራሮችን የመዘርጋት ሥራ መጀመሩን ነው የገለጹት፡፡

"ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትና አደጋውን ለመቀነስ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት የሚቆይ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ በተያዘው ዓመት ትግበራው ተጀምሯል" ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት የትግበራው አንዱ አካል የሆኑት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራና የንቅናቄ መድረኮች በየአካባቢው እየተካሄዱ ነው፡፡

ለማህበረሰቡም አማራጭ የልቅ ግጦሽና የሰፈራ ቦታ፣ የማገዶ፣ የኃይል አቅርቦትና ሌሎች አማራጮች በቀጣይ እንዲቀርቡለት የማድረግ ስራም እንደሚሰራ አመለክተዋል፡፡

ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች እየተዘጋጁ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

ብሔራዊ ፓርኮች የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲሆኑና የአካባቢው ህብረተሰብ ከዚህ በዘላቂነት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ እንደሚሰራም አቶ ኩመራ ተናግረዋል።

የአካባቢ ደንና አየር ንበረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ በበኩላቸው እንዳሉት በብሔራዊ ፓርኮች፣ በጥብቅ ደኖችና በውሃ አዘል መሬቶች ላይ እየደረሰ ያለው ውድመት ለከፋ ችግር የሚያጋልጥ ነው።

ከደን መመናመንና ከመሬት መራቆት ጋር በተያያዘ እየተስተዋለ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ መዛባት በሀገሪቱ ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያስከተለ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኮሚሽነሩ እንዳሉት በሀገሪቱ የሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች፣ ጥብቅ ደኖችና ለስነ-ምህዳሩ ተስማሚ የሆኑ ሥፍራዎች እየደረሰባቸው ካለው ጥፋት ለመታደግ ባለድርሻ አካላት የተጠናከረ ጥበቃ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

የተራቆቱ አካባቢዎችን በሀገር በቀል የደን ዝርያዎች መልሶ በመሸፈንና ተንከባክቦ በማሳደግ እየተዛባ የመጣውን ስነምህዳር ለማስተካከል ኮሚሽኑ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። 

በሀገሪቱ የሚገኙ 27 ብሔራዊ ፓርኮችና ሁለት የዱር እንስሳት መጠለያ ስፍራዎችን ጨምሮ ጥብቅ ቦታዎች እንዲሁም በባዮስፌርና በሌሎች የተሸፈኑ ሥፍራዎች ከሀገሪቱ ጠቅላላ ስፋት 8 ነጥብ 5 በመቶ ያህሉን እንደሚሸፍን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም