እንግሊዝ በኢትዮጵያ ለመጣው ለውጥ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች

41

አዲስ አበባ የካቲት 12/2011 እንግሊዝ በኢትዮጵያ ለመጣው ሁሉን አቀፍ ለውጥ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የአገሪቷ አምባሳደር ገለጹ።

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የእንግሊዝ አምባሳደር ዶክተር አልስቴር ዴቪድ ማክፔልን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይታቸውም አምባሳደር ማክፔል እንዳሉት እንግሊዝ በኢትዮጵያ የመጣውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ በመደገፍ ድጋፏን አጠናክራ ትቀጥላለች።  ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላም እንዲሰፍን እየተጫወተችው ያለውን ሚናም አገራቸው እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል።

አምባሳደሩ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሁለቱን አገሮች የቆየ ወዳጅነትና ትብብር አጠናክረው ለማስቀጠል እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

እንግሊዝ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ልማት በገንዘብ ከሚደግፉ አገሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው ሁለቱ አገሮች በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን ተመሳሳይ ራዕይ ያላቸው በመሆኑ በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ በማሳደግ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት በትብብር እንደሚሰሩም ገልጸውላቸዋል።

በአገሮቹ መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ፣ የምጣኔ ሀብት እና የባህል ትስስር ለማሳደግ በትብብር እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ እና ስለተመዘገቡ ውጤቶች እንዲሁም ያጋጠሙ ተግዳሮቶች በተመለከተም ዶክተር ወርቅነህ ለአምባሳደሩ ገለጻ አድርገውላቸዋል።

እንግሊዝ ለኢትዮጵያ እያደረገችው ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በተመለከተ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አትዮጵያና እንግሊዝ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሰረቱት በ1889 ዓ.ም ሲሆን በበርካታ ጉዳዮች ላይ በትብብር በመስራት ላይ እንደሚገኙ የሚኒስቴሩ መግለጫ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም