በኢትዮጵያ ወጥነት ያለው የካንሰር ህክምናን ለመስጠት የሚያስችል መመሪያ ተግባራዊ ሆነ

55

አዲስ አበባ የካቲት 12/2011  በኢትዮጵያ ወጥነት ያለው የካንሰር ህክምናን ለመስጠት የሚያስችል የተቀናጀ የካንሰር ህክምና መመሪያ ተግባራዊ መሆኑ ተገለፀ።

በተያዘው ወር ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያና ናይጄሪያ ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት የሚተገብሩትን የተቀናጀ የካንሰር ህክምና መመሪያ  አፅድቀው ነበር።

በዛሬው እለትም የአሜሪካ የካንሰር ሶሳይቲ ከጤና ሚኒስቴርና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በተቀናጀ የካንሰር ህክምና መመሪያ ላይ አውደ ጥናት አካሂዷል።

 በጤና ሚኒስቴር የካንሰር መከላከልና መቆጣጠር አማካሪ ዶክተር ኩኑዝ አብደላ በዚሁ ወቅት እንዳሉት መመሪያው አለም አቀፍ ይዘት ያለውና ለሀገሪቷ በሚስማማ መልኩ ተቃኝቶ የተወሰደ ነው ብለዋል።

መመሪያው  በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚገኝ ሲሆን የጤና ባለሙያዎች እንዲማሩበት እንደሚደረግም ነው ዶክተር ኩኑዝ ያብራሩት።

የተዘጋጀው መመሪያ ሁሉም ባለሙያ ተመሳሳይ የሆነ ግንዛቤ ኖሯቸው ሳይንሱን በተከተለና ሌሎች አለማት በደረሱበት ደረጃ የህክምና አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችላቸው ነውም ብለዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ግርማ አሸናፊ በበኩላቸው "የካንሰር ህሙማን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም የሚያገኙት ህክምናና የባለሙያዎች ቁጥር ውስን" መሆኑን ይናገራሉ።

መመሪያው ፀድቆ ወደስራ መግባቱም ጥራት ያለው የካንሰር ህክምና ለመስጠትና በካንሰር ዙሪያ ከሚሰሩ ድርጅቶችና ከአፍሪካ ሀገራት ጋርም በትብብር ለመስራት ያስችላል ነው ያሉት።

ከዚህ በፊት የካንሰር ህክምና እየሰጡ ያሉና ህክምናውን የሚጀምሩ የጤና ተቋማት ወጥነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡና የህክምና ባለሙያዎችም መመሪያውን መሰረት ያደረገ ትምህርት እንዲሰጡ ያስችላል።

በአሜሪካ የካንሳር ሶሳይቲ የዓለም ካንሰር ህክምና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶክተር ሜግ ኦ ብሬይን በበኩላቸው መመሪያው ደረጃውንና ጥራቱን  የጠበቀ የካንሰር ህክምና ለመስጠት ያግዛል።    

ከዚህም በተጨማሪ የአፍሪካ ሀገራት በቅንጅት የካንሰር ህክምናን ለመስጠት እንዲሁም ለመከላከል ይረዳቸዋልም ብለዋል።  

በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የሰው ኃብትና የግብዓት እጥረት ያለባቸው በመሆኑ መመሪያው ያላቸውን ጥቂት ሀብት በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ያስችላል ሲሉም ገልጸዋል። 

በሁሉም የአለም ሀገራት የካንሰር በሽታ ስርጭት እየጨመረ መሆኑን የገለፁት ዶክተር ሜግ በአፍሪካም የታማሚውን ቁጥር ያገናዘበ ህክምና ለመስጠት መመሪያው ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል። 

መመሪያው ወጥነት ያለው የካንሰር ህክምናን ለሁሉም ለመስጠትና በሽታውን ለመከላከል እንደሚያግዝም አብራርተዋል።

የአሜሪካ ካንሰር ሶሳይቲ ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ባለሙያዎችን እንደሚያሰለጥንና ታማሚዎች ህክምና እንዲያገኙ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ 67 ሺህ አዳዲስ የካንሰር ህሙማን ቢመዘገቡም የህክምና አገልግሎት እያገኙ ያሉት ከ12 ሺህ የማይበልጡት መሆናቸውም ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም