የአምቦ ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒዬን 200 የተቸገሩ ህፃናትን እያስተማረ ነው

62

አምቦ የካቲት 12 / 2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን የአምቦ ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒዬን 200 የተቸገሩ ህፃናትን እያስተማረ መሆኑን ገለጸ።

ተማሪዎቹ ድጋፉ ትምህርታችንን በአግባቡ እንድንከታተል ረድቶናል ይላሉ፡፡

የዩኒዬኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጋሮምሣ ባይሣ እንደተናገሩት ዩኒዬኑ በዞኑ በሚገኙ ስምንት ወረዳዎች የተቸገሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እያደረገ ነው ።

ቶኬ ኩታዬ፣ ዳኖ ፣ አምቦ ፣ ጀልዱና ደንዲ ተማሪዎቹ ከሚረዱባቸው ወረዳዎች መካከል ናቸው ፡፡

ዩኒዬኑ ለተማሪዎቹ  ድጋፍ በየዓመቱ በአማካይ 300 ሺህ ብር በጀት እየመደበ መሆኑን አስረድተዋል።

ተማሪዎቹ ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስም ድጋፉን እንደሚቀጥል ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ዩኒዬኑ ከ 2001 ጀምሮ ለድጋፉ  ከ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም አስታውቀዋል ።

የጉደር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ዮናታን ፊርሣ በሰጠው አስተያየት ቤተሰቦቹ የዕለት ምግብ ከማሟላት ባለፈ ወጪውን ሸፍነው ለማስተማር አቅም የላቸውም ፡፡

ሆኖም ዩኒዬኑ አንደኛ ክፍል ከገባበት ጊዜ አንስቶ የደብተር፣ የዩኒፎርምና  የስክሪፕቶ ድጋፍ ባያደርግለት ኖሮ፤ አሁን ላለበት ደረጃ ለመድረስ ይቸገር እንደነበር ገልጿል፡፡

"ለወደፊቱ ጠንክሬ በመማር ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሼ ለእኔ በተደረገልኝ ዕርዳታ መሠረት ሌሎች ወገኞቼን ለመርዳት ዓላማ አለኝ " ሲል ዮናታን ተናግሯል፡፡

ሌላዋ በአምቦ ወረዳ የሜጢ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ  ደሜ ተፈሪ በበኩሏ ከአራት ዓመታት በፊት ወላጆቿ ለትምህርት የሚያስፈልጋትን ቁሳቁስ ባለማሟላታቸው ከትምህርት ገበታዋ ልትለያይ የደረሰችበትን ሁኔታ ታስታውሳለች፡፡

ዩኒዬኑ ከ 2008 ጀምሮ እያደረገላት ባለው የዩኒፎርም፣ የጫማና የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አሁን ላለችበት ደረጃ መድረሷን ገልጻለች።

ወደፊትም በሚደረግላት ድጋፍ ታግዛ በመማር ቤተሰቦቿን ከድህነት የማላቀቅ ዓላማ እንዳላት ደሜ አስረድታለች፡፡

"ዩኒዬኑ ባደረገልኝ ድጋፍ ትምህርቴን በሚገባ እየተከታተልኩ እገኛለሁ። በሚቀጥለው ዓመት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ስለምሸጋገር ድጋፋቸው በዚሁ መልኩ እንዲቀጥል እጠይቃለሁ" ያለው ደግሞ በአምቦ ወረዳ የስምንተኛ ክፍል ተማሪው አብዲሣ ፉፋ ነው፡፡ 

የአምቦ ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒዬን ከ121 ሺህ በላይ አባላት አሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም