የፌዴራል ስርዓቱ ለድርድር አይቀርብም- ኦዴፓ

64

አዲስ አበባ የካቲት 12/2011 የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) በፌዴራሊዝም ስርዓቱ ላይ ከማንም ጋር ለድርድር እንደማይቀመጥ ገለጸ።

ፓርቲው ባወጣው መግለጫ በአጀንዳነት ይዞ ከሚታገልባቸው ጉዳዮች ውስጥ ዋነኛው የፌዴራል ስርዓቱ መሆኑንም አመልክቷል።

ለፌዴራል ስርዓቱ መምጣት ከፍተኛ ዋጋ ተከፍሎበታል ያለው ፓርቲው ስርዓቱ ለድርድር የማይቀርብ መሆኑንም አስታውቋል በመግለጫው።

በአሁኑ ወቅት በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የፌዴራል ስርዓቱን ሊያፈርስ እንደሆነ እንዲሁም ህብረተሰቡ በፌዴራል ስርዓት ላይ ያለውን እምነት እና ተስፋ እንዲቀንስ ከፍተኛ የሆነ የሀሰት ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑንም ገልጿል።

የሀሰት ዘመቻው ሁለት ዓላማ ያለው ነው ያለው ኦዲፒ ከእነዚህም አንደኛው የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች አሁን ያለውን ለውጥ በጥርጣሬ እንደሚመለከቱ ማድረግ ነው ብሏል።

በዚህም የራሳቸውን ባህል፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ታሪክ ማሳደግን በትግል እና በመስዋእትነት ያገኙ ብሄሮችና ብሄረሰቦች የፌዴራል ስርዓቱ ሊፈርስ ነው በሚል በጥርጣሬ ተቃውሞ እንዲያስነሱ ታስቦ የሚደረግ ሴራ መሆኑንም ገልጿል።

የኦሮሞን ህዝብ “ተጨማሪ መብት ማግኘትህ ቀርቶ ከዚህ ቀደም የተገኘውን መብት ልታጣ ነው” በሚል በማደናገር እርስ በርስ ለማጋጨት ያለመ መሆኑንም አስታውቋል።

"የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ለመመለስ ይሰራል" ያለው መግለጫው የአዲስ አበባ እና የአፋን ኦሮሞ ጉዳይም በትኩረት እየተሰራበት ያለ መሆኑን አመልክቷል።

ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች ላይም ትኩረት በመስጠት እየተሰራበት መሆኑን አስታውቋል።

"ኦዲፒ ለተጨማሪ ድል ይሰራል እንጂ ከዚህ ቀደም የተገኙ ድሎችን በምንም መልኩ አያጨናግፍም" ያለው መግለጫው በፌዴራል ስርዓቱ ላይ ከማንም ጋር ለድርድር እንደማይቀመጥም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም