የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፈርቲሊቲና የስነ ተዋልዶ ህክምና አገልግሎት የህግ ማእቀፍ ሊኖረው ይገባል

628

አዲስ አበባ የካቲት 12 / 2011በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የተከፈተው የፈርቲሊቲና የስነ ተዋልዶ ህክምና ማዕከል በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ግልጽ የሆነ ህግ ሊኖረው እንደሚገባ አንድ የህግ ባለሙያ ገለጹ።

ኮሌጁ በበኩሉ ከሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚነሱ የህግ ጥያቄዎችን ለመመለስ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል።

ማዕከሉ ከሴቷ እንቁላል እና ከወንዱ ዘር በመውሰድ ከማህጸን ውጪ ልጅ እንዲፈጠር በማድረግ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ጽንሱን በሴቷ ማህጸን ውስጥ በማስቀመጥ የሚከናወን የህክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ማስታወቁ ይታወሳል።

የህግ ባለሙያዋ ወይዘሮ በልዩ እስጢፋኖስ እንዳሉት በኢትዮጵያ በኪራይ ወይም በበጎ ፈቃድ በሌላ ሴት ማህጸን ውስጥ ጽንስን አሳድጎ ወላጅ ለመሆን የሚያስችል በግልጽ የሚፈቅድ ህግ የለም።

እንዲሁም በኪራይም ሆነ በበጎ ፈቃድ የሌላ ሴትን ማህጸን አለመጠቀም ክልከላ ላይ የአተረጓጎም ጥያቄዎች እንዳሉም አስረድተዋል። 

በሴት ማህጸን ውስጥ ጽንስን ከማስቀመጥ በተጨማሪ በተለያየ ምክንያት ማህጸናቸው ጽንስ መሸከም ከማይችሉ ሴቶች እንቁላል ተወስዶ በላብራቶሪ የተወሰነ ዕድገት እንዲያገኝ ከተደረገ በኋላ በሌላ ሴት ማህጸን ውስጥ ማስቀመጥ በሌሎች አገሮች ተሞክሮ እንዳለ ወይዘሮ በልዩ አስረድተዋል። 

በቤተሰብ ህጉ የተደነገገው ''እናት ማለት ልጅ የወለደች ብቻ ስትሆን'' በማህጸን ኪራይም ሆነ በሌላ መንገድ እናት መሆን እንደማይቻል የገለጹት የህግ ባለሙያዋ ከማህበረሰቡ ችግር አኳያ በህክምና አገልግሎት ልጅ ማግኘት ይችላሉ የሚል ሌላ ትርጓሜ እንደሚሰጠውም ተናግረዋል።

እስከ አሁን ድረስ ከእናትነት ጋር በተያያዘ ያጋጠመ የህግ ትርጓሜ ችግር የሌለ ቢሆንም በመንግስት በተከፈተው የፈርቲሊቲና የስነ ተዋልዶ ህክምና ማዕከል አገልግሎት ጋር በተያያዘ የተለያዩ የህግ ጥያቄዎች ሊነሱ ስለሚችሉ የህግ ማዕቀፍ አስቀድሞ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ነው የህግ ባለሙያዋ ያስገነዘቡት።

"ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ በሚነሳ ጭቅጭቅ የሚወጣ ህግ አንዳንዴ የቀጪነት ዓላማ ነው የሚኖረው" ሲሉ የህግ ባለሙያ ወይዘሮ በልዩ ተናግረዋል። 

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፈርቲሊቲና ስነ ተዋልዶ ማዕከል ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሰናይት በየነ በበኩላቸው የጤና ሚኒስቴር እያዘጋጀ ባለው የጤና ህግጋት ላይ የመካንነት ህክምና ህግና መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

ልጅ መውለድ አለመቻል ማለት ጥንዶች ለአንድ ዓመት መደበኛ የግብረ ስጋ ግንኙነት አድርገው ሴቷ ማርገዝ ሳትችል ሲቀርና ችግሩ በህክምና መዳን የሚችልና የማይችል ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ሁለቱ ጥንዶች ምርመራ አድርገው የችግሩ ምንጭ የማይታወቅበት አጋጣሚም እንዳለ የገለጹት ዶክተር ሰናይት፤ ይህ ህክምና ጥንዶቹ ልጅ እንዲኖራቸው በቴክኖሎጂ የታገዘ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።

ሙሉ የህክመና አገልግሎቱን አግኝቶ የእርግዝና ምርመራ ለማድረግ እስከ ሦስት ወር ድረስ የሚወስድ ሲሆን ችግሩ አለብን ብለው የሚጠራጠሩ ጥንዶች በማንኛውም የህክምና ተቋም ምርመራ ካደረጉ በኋላ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፈርቲሊቲና ስነ ተዋልዶ ማዕከል ቢመጡ የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት እንደሚፋጠን ዶክተር ሰናይት አስረድተዋል።

በታዳጊ አገሮች በተፈጥሮ መንገድ ልጅ መውለድ የማይችሉ ጥንዶች ከ10 እስከ 15 በመቶ እንደሚሆኑ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ለመጀመሪያው ጊዜ በመንግስት ሆስፒታል ውስጥ የተጀመረው የፈርቲሊቲና የስነ ተዋልዶ ህክምና አገልግሎት ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 35 ዓመት ድረስ ለሚገኙ ጥንዶች የሚሰጥ የህክምና አገልግሎት ነው።

የፈርቲሊቲና የስነ ተዋልዶ ህክምና ማዕከል የካቲት 3 ቀን 2011 ዓ.ም ተመርቆ ስራ መጀመሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም