ፋብሪካው በኤለክትሪክ እጦት ምክንያት ሥራ ለማቆም መገደዱን አስታወቀ

65

አሶሳ የካቲት 12/2011 የአሶሳ ገበሬዎች ዩኒዬን የምግብ ዘይት  ፋብሪካ ባለፉት ሶስት ወራት በኤሌክትሪክ እጦት ሥራ ለማቆም መገደዱን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ቅርንጫፍ በዚህ ሳምንት ችግሩ ይፈታል ብሏል፡፡

የፋብሪካው ተወካይ አቶ አባተ አሰፌ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ፋብሪካው በትራንስፎርመር ብልሽት ሥራ በማቆሙ አምስት ሚሊዮን ብር ያህል ገቢ አጥቷል።

ፋብሪካው በሩብ ዓመቱ 60 ሺህ ሊትር ዘይት ለማቅረብ የነበረው ዕቅድ መስተጓጎሉን አመልክተዋል፡፡

ዩኒዬኑ ለፋብሪካው ግብዓት የሰበሰበው 2 ሺህ ኩንታል ያህል ሰሊጥና ኑግ በክምችት ላይ በመቆየቱ  ለብልሽት መዳረጉን አስታውቀዋል፡፡

ምርቱን ከአካባቢው አልፎ ለማዕከላዊ ገበያና ለክልሎች ያቀርብ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አባተ፣ ፋብሪካው ሥራ በማቆሙ ደንበኞችን እያጣ  መሆኑንም አስረድተዋል።

ችግሩ በዚህ ከቀጠለ ፋብሪካው ሠራተኞቹን ለማሰናበት ይገደዳል ብለዋል።

ፋብሪካው ባለ 200 ኪሎ ቮልት ትራንስፎርመር ለማስገባት 370 ሺህ ብር ክፍያ መፈጸሙን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ቅርንጫፍ ሀላፊ አቶ ካሣሁን ከበደ ለፋብሪካው አገልግሎት የሚሰጠው ባለ 100 ኪሎ ቮልት ትራንስፎርመር ሲበላሽ በወቅቱ ሳይተካ የቀረው በትራንስፎርመር እጥረት እንደሆነ ተናግረዋል።

በቅራንጫፍ ጽህፈት ቤቱና በዩኒዬኑ ማለቅ የነበረባቸው ሥራዎች በወቅቱ ባለመጠናቀቃቸው ምክንያት ዩኒዬኑ ያቀረበውን የ200 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በወቅቱ እንዳላቀረበ ገልጸዋል።

ዩኒዬኑ ለተለዋጩ ትራንስፎርመር ክፍያውን የፈጸመው በቅርቡ መሆኑን ያስታወቁት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ፣ በዚህ ሳምንት ትራንስፎርመር ተተክሎ አገልግሎት ይጀምራል ብለዋል።

ዩኒዬኑ በ87 ሺህ ብር  መነሻ ካፒታል ሥራውን የጀመረው በ1997 ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ጠቅላላ ካፒታሉ 24 ሚሊዮን ብር  ደርሷል፡፡

ዩኒዬኑ በ60 መሠረታዊ ማህበራት ሥር የታቀፉ 17 ሺህ 634 አርሶ አደር አባላት አሉት።

የአካባቢውን የምግብ ዘይት ፍላጎት ለማሟላት ዩኒዬኑ በከተማው የዘይት ፋብሪካውን የከፈተው በ2003 ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም