የጤና ባለሙያዎችና የባዮ-ሜዲካል ቴክኒሻኖች አቅም ማጎልበቻ መርሃ ግብር ይፋ ሆነ

63

አዲስ አበባ የካቲት 12/2011 በኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎችና የባዮሜዲካል ቴክኒሻኖችን አቅም የሚያጎለብት የሶስት ዓመት መርሃ ግብር በጀርመን መንግስት የልማት ድርጅት ይፋ ሆነ።

13 ሚሊዮን ዩሮ የተበጀተለት ፕሮጀክቱ እንደ አውሮፓዊያን የዘመን ቀመር እስከ 2021 ይዘልቃል።

የልማት ድርጅቱ ከጤና እና ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴሮች ጋር በመተባበር የህክምና መሳሪያዎች አጠቃቀም ማሻሻያ መርሃ ግብሩን ትናንት በአዲስ አበባ ይፋ አድርጓል።

በኢትዮጵያ የድርጅቱ ዳይሬክተር ፒተር ፓለስች ከኢትዮጵያ ጋር በግብርና፣ በጤና፣ በብዝሃ ህይወት፣ በትምህርትና በምግብ ዋስትና ዘርፎች በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ነቀምት ሆስፒታል ይፋ የተደረገው የህክምና ባለሙያዎች መሳሪያዎችን ጥቅም ላይ እንዲያውሏቸው የሚያስችል የአቅም ግንባታ መርሃ ግብርም የትብብሩ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሆስፒታሎችን ጨምሮ በሁሉም የህክምና ተቋማት ከሚገኙ የህክምና መሳሪያዎች 50 በመቶ ያህሉ አገልግሎት እንደማይሰጡ ጠቁመዋል።

በአገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች የጤና ተቋማትም 70 በመቶ ያህሉ የህክምና መሳሪያዎች በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎት አይሰጡም።

በመሆኑም 'በጥገና አቅም ውስንነት፣ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ባለመላመድና በግብዓት እጥረት ሳቢያ አገልግሎት የማይሰጡ የህክምና መሳሪያዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል የቴክኒክ ስልጠና እንሰጣለን' ብለዋል።

ከህክምና ተቋማት ባለሙያዎች ባሻገር በከፍተኛ ትምህርትና በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ማዕከላት ጭምር የባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በጤና ሚኒስቴር የህክምና አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ያዕቆብ ሰማን በበኩላቸው መርሃ ግብሩ መንግስት የጀመረውን የህክምና ባለሙያዎች አቅም ግንባታ ስራ 'ያጠናክረዋል' ብለዋል።

በኢትዮጵያ በጤና ባለሙያዎችና የባዮ-ሜዲካል ቴክኒሻኖች ላይ የሚስተዋለውን የህክምና መሳሪያዎች በአግባቡ የመጠቀም ክፍተት እንደሚሞላም ገልጸዋል።

በየጤና ተቋማቱ የሚገኙ የህክምና መሳሪያዎች ከውጭ አገር በውድ ዋጋ ተገዝተው ቢገቡም ለረዥም ጊዜ ጥቅም ላይ ሳይውሉ ይቆያሉ።

ይህም ዜጎች ማግኘት የሚገባቸውን የተሟላ የህክምና አገልግሎት እንዳያገኙ ከማድረግ ባለፈ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።

የጤና ሚኒስቴር ችግሩን በመረዳት የህክምና መሳሪያዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋላቸውን የሚከታተል ዳይሬክቶሬት በማቋቋም ልምድ ካላቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የጀርመን መንግስት የልማት ድርጅትም የዚሁ አካል መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ያዕቆብ ለመርሃ ግብሩ ውጤታማነት 'መንግስት አስፈላጊውን ክትትል ያደርጋል' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም