የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ለተፈናቃዮች የ25 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

100

ባህርዳር የካቲት 11/2011 የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የሚውል የ25 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን የለውምወሰን ዛሬ ድጋፉን ለክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት ድጋፉ ተጎጅዎችን መልሶ ለማቋቋም ይውላል።

እርዳታው ተፈናቃዮች መልሶ ለማቋቋምና ወደ ቀደመ ህይወታቸው ለመመለስ የክልሉ ሀብት የሆነው አብቁተ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ሲል ያደረገው ድጋፍ መሆኑንም ተናግረዋል።

ተቋሙ  ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቁት ዋና ዳይሬክተሩ ከችግሩ ስፋት አንጻር ሌሎች ግለሰቦችና ተቋማት ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አማረ ክንዴ በበኩላቸው በክልሉ በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር እንዲሁም ከሌሎች ክልሎች 88 ሺህ 450 የክልሉ ተወላጆች መፈናቀላቸውን ተናግረዋል።

ተፈናቃዮችን  በ13 ጣቢያዎች እንዲሰፍሩ በማድረግ የዕለት ምግብ፣ አልባሳትና የመመገቢያ ቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም አመልክተዋል።

ተፈናቃዮችን ዘላቂነት ባለው መንገድ መልሶ ለማቋቋም ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ድጋፍ የማስተባበር ስራ መጀመሩን ጠቅሰው አብቁተ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የአማራ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት  ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማሃኝ አስረስ በበኩላቸው ተፈናቃዮች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ጫና እንደደረሰባቸው ገልጸው ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ተፈናቃዮችን በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ መልሶ ለማደራጀትና ወደ ቀደመ ህይወታቸው ለመመለስ መርሀግብር ወጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም