በሕገ ወጥ ንግድና በግብር ፍትሃዊነት የሚታዩ ችግሮችን መፍታት ይገባል- የደቡብ ክልል ግብር ከፋዮች

65

ሀዋሳ የካቲት 11/2011 በሕገ ወጥ ንግድና በግብር ፍትሃዊነት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ እንደሚገባ የደቡብ ክልል ግብር ከፋዮች ገለጹ።

በገቢ አሰባሰብ ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራ የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን አስታውቋል።

በክልሉ ጉራጌ ዞንና ሐዋሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ግብር ከፋዮች እንደገለጹት በግብር ትመና፣በተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያ፣ ፍትሃዊነትና ግብር በታማኝነት ከመክፈል አንጻር ችግሮች በስፋት ይታያሉ።

ችግሮቹን በመፍታትም ሕገ ወጥ ንግድንና ፍትሃዊ ያልሆነ የግብር አጣጣል ችግሮችን የሚያስቀር ስልት መቀየስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ በሆቴል ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ ፍቃዱ አሶሬ ከግብር ክፍያ ጋር ተያይዞ የፍትሃዊነት ችግሮች መኖራቸውን ይናገራሉ።

ከፍተኛ ግብር መክፈል የሚገባቸው ነጋዴዎች እያሉ በመንገድ ላይ የጀበና ቡና የሚሸጡትን ግብር የሚከፍሉበትን ሁኔታ መኖሩንም ለአብነት ያቀርባሉ።

ሕገ ወጥ ንግድ በህጋዊ ነጋዴው ላይ የሚያሳድረው ተዕእኖ መኖሩን ያመለከቱት አቶ ፈቃዱ፣ በሕጋዊ ንግድ ሽፋን ሕገ ወጥ ሥራ የሚያከናውኑ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል ብለዋል።

ከተጨማሪ እሴት ታክስ ጋር በተያያዘም ሽያጫቸው ከፍተኛ የሆኑ ነጋዴዎች የሚፈለግባቸውን እንዲከፍሉ መደረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።

በታሸገ ውሃ ማምረትና ሽያጭ የተሰማሩትና የደቡብ ክልል የታክስ አምባሳደር ኢንጂነር ዘላለም ወልደ አማኑኤል በበኩላቸው "ግብር እኔንም ሁሉንም የሚመለከት የጋራ ጉዳያችንና ራሳችን ለራሳችን የምንከፍለው ነው" ብለዋል።

ነጋዴው ማህበረሰብ በሚያገኘው ገቢ ልክ የሚጠበቅበትን ግብር የመክፈል ግዴታውን እንዲወጣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ቢሰሩም፤ በቂ እንዳልሆኑ ጠቁመዋል።

"በዓመት እስከ 20 ሚሊዮን ብር ግብር በመክፈል በክልል ደረጃ በተደጋጋሚ ሞዴል ግብር ከፋይ በመባል የዋንጫ ተሸላሚ ነኝ" ያሉት ኢንጂነር ዘላለም፣ በዚህም የክልሉ መንግሥትና የገቢዎች ባለስልጣን የታክስ አምባሳደር አድርጎ እንደሾማቸው ተናግረዋል።

በግብር አከፋፈል ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ባለስልጣኑ በትኩረት መስራት እንደሚገባው አመልክተዋል።

በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ የእዣ ሆቴል የሂሳብ ሠራተኛ ወጣት ሰላማዊት ወርቁ በበኩሏ ከፍተኛ ግብር ከሚከፍሉ ነጋዴዎች የሚጠበቀው ግብር እንደማይሰበሰብ መታዘቧን ተናግራለች።

ከግብር ግመታ ጋር በተያያዘ በትመና ወቅት ላይ የሚነሳ ቅሬታ የፍትሃዊነት ጥያቄ እንደሚያስነሳ ጠቁማለች።

በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመቆጣጠሪያ ሥርዓት አለመኖሩ የግብር ሥርዓቱ ፍትሃዊ እንዳይሆን ማድረጉን ሰላማዊት ገልጻለች።

የደቡብ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሴ አስረስ ከግብር ከፋዩ የሚነሱት ችግሮች ትክክለኛ መሆናቸውን አምነው ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮችን በመለየት ማስተካከያ መደረጉን ተናግረዋል።

በግብር ስወራ፣ ማጭበርበርና  ከተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያ ጋር በተያያዘ በጥናት ላይ የተመሰረተ በአጥፊዎች ላይ እርምጃ የሚወሰድበት ሥርዓት መዘርጋቱን ጠቁመዋል።

ከግብር ግመታ ጋር በተያያዘ የደረጃ ''ሐ''ግብር ከፋዮችን የሚመለከት መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የግብር ትመናው በየዓመቱ እንደሚተመን ተደርጎ መቅረቡ  አግባብነት የለውም ብለዋል።

የደቡብ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን በተያዘው የበጀት አመት 11 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዷል። እስከ በጀት ግማሽ ዓመቱ አጋማሸ ድረስ  ከ3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም