በአክሱም መስማት ለተሳናቸው ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ነጻ ሕክምና ተሰጠ

91

አክሱም የካቲት 11/2011 በአክሱም ከተማና አካባቢው መስማት ለተሳናቸው ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ነጻ የሕክምና አገልግሎትና የመሳሪያ ድጋፍ ተሰጠ።

ድጋፉ የተሰጠው አክሱም ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል እና ‘‘ከስታርኪ ሂሪንግ ፋውንዴሽን‘‘ የተባለ ዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅት ባደረጉት ትብብር ነው።

የዩኒቨርሲቲው ሪፈራል ሆስፒታል ኃላፊ ዶክተር አሮን ወልደገብርኤል ለኢዜአ እንደገለፁት ባለፉት ሁለት ቀናት ለሰዎቹ የህክምና አገልግሎት የተሰጠው ከውጭ በመጡ የህክምና ቡድን አባላት አማካኝነት ነው ።

በእዚህም በኢንፌክሽንና ነርቭ ጉዳት ሳቢያ የመስማት ችግር የነበረባቸውን አንድ ሺህ ህሙማን የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በነፍስ ወከፍ የጆሮ ማዳመጫ መሳሪያ በድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል።

"ሆስፒታሉ ወደፊትም ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ ድርጅቶችና ባለሙያዎችን በማፈላለግ ተመሳሳይ የህክምና አገልግሎት ይሰጣል" ብለዋል።

እንደ ዶክተር አሮን ገለጻ ሪፈራል ሆስፒታሉ በዚህ ዓመት ብቻ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የማህጸን ማስወገድ፣ የዓይን ሞራ ግርዶሽና የቆዳ ጤና ችግር ለነበረባቸው 2 ሺህ ሰዎች ነጻ የህክምና አገልግሎት ሰጥቷል ።

በአሜሪካ የፋውንዴሽኑ የልኡካን ቡድን አስተባባሪ ዶክተር ጠዓመ እምባዬ በበኩላቸው ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ በስምንት ዙር 8 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች ተመሳሳይ የህክምና አገልግሎት መስጠቱን ነው የገለጹት።

"ከአሜሪካ የመጣነው የህክምና እርዳታ ለማድረግ ነው" ያሉት ዶክተር ጠዓመ በመቀሌ፣ በጅማና በድሬዳዋ ከተሞች ተመሳሳይ የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

"አንድ መስማት የተሳነው ሰው የህክምና የጆሮ ማዳመጫ ለማግኘት እስከ 20 ሺህ ብር ወጪ ይጠይቀዋል" ያሉት ደግሞ በዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ከአንገት በላይ የህክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ዘነበ ናቸው ።

ፋውንዴሽኑ ለጆሮ ህሙማኑ ያደረገው ድጋፍ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል ።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል የሑመራ ከተማ ነዋሪ ወጣት መርሃዊት ገብረዋህድ "በተደረገልኝ ነጻ የጆሮ ህክምና መስማት ችያለሁ" ብላለች።

ከዚህ በፊት ምንም አይነት ድምጽ ትሰማ እንዳልነበር ገልጻ በአሁኑ ወቅት ከሩቅ ድምጽ መስማት በመቻሏ ደስተኛ መሆኗን ተናግራለች።

የናዕዴር ዓዴት ወረዳ ነዋሪ ቄስ ኃይለማርያም ተክሉ በበኩላቸው ላለፉት አምስት ዓመታት በሁለት ጆሯቸው የመስማት ችግር ገጥሟቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

በሆስፒታሉ ህክምና የማዳመጫ መሳሪያ ተገጥሞላቸው መስማት እንደቻሉ በመግለፅ አገልግሎቱን ለሰጧቸው አካላት ምስጋና አቅርበዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም