የፑንዱኒያ ሰው ሰራሽ ደን በህገ-ወጥ ጭፍጨፋ ጉዳት እየደረሰበት ነው

67

ሶዶ የካቲት 11 / 2011 በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኘው የፑንዱኒያ ሰው ሰራሽ የባህር ዛፍ ጥብቅ ደን በህገ-ወጥ ጭፍጨፋ ምክንያት ለጉዳት መዳረጉን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።

ደኑን ከውድመት ለመከላከል ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደተግባራዊ ሥራ መገባቱን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።

በዞኑ የኦፋ ጋንዳባ ቀበሌ ነዋሪ መቶ አለቃ ዳዊት አቦታ ለኢትዮዽያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት  ደኑ በህዝብና በመንግስት ተሳትፎ ለዓመታት ተጠብቆ ቆይቷል።

ከሁለት ዓመት ወዲህ የደኑ ይዞታ በፍጥነት እየተመናመነ መጥቶ ወደ መጥፋት በመቃረብ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በደኑ ላይ ይደርሰ የነበረውን ጭፍጨፋ ህብረተሰቡ ለመከላከል ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሱት መቶ አለቃ ዳዊት፣ በአሁኑ ሰዓት በደኑ ላይ አየተፈጸመ ያለው ህገ-ወጥ የደን ጭፍጨፋ ከአካባቢው ነዋሪ ህብረተሰብ አቅም በላይ መሆኑን አስረድተዋል።

ከአምስት ዓመት በፊት በደኑ የጥበቃ ሠራተኛ ሆነው ማገልገላቸውን የተናገሩት በዞኑ የአዲሱ ኦፋ ሴሬ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጴጥሮስ እንድሪያስ በበኩላቸው የደኑ ጠባቂዎች ቁጥር በቂ ባይሆንም በአካባቢው ህዝብና በመንግስት የተሻለ ድጋፍ ይደረግ እንደነበር አስታውሰዋል።

ማንነታቸው የማይታወቁ ግለሰቦች ህጋዊ ፈቃድ እንዳላቸው አድርገው በደኑ ውስጥ ሠራተኛ  በማሰማራት ዛፎቹን እየቆረጡ ግንዱን በመኪና ጭነው ሲያወጡ ማየት የተለመደ ተግባር እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል።

አቶ ጴጥሮስ እንዳሉት የደን ጭፍጨፋውን የሚያከናውኑ ግለሰቦች ዛፍ አቆራረጣቸው ተክሉ  መልሶ እንዲያቆጠቁጥ በሚያስችል መልኩ ስላልሆነ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል።

“የአካባቢው ነዋሪዎች ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ብናሳውቅም ምንም ምላሽ የሚሰጥ አካል አለመኖሩ ድርጊቱን ተባብሶ እንዲቀጥል አድርጓል” ብለዋል።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደኑ በህዝቡና በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶት በመጠበቁ የአካባቢው የአየር ሚዛን እንዳይዛባ ያበረከተው አስተዋጽኦ የጎላ እንደነበር የገለጹት ደግሞ በዞኑ የደን ብዝሃ ህይወት ባለሙያ አቶ በርገነ ቢጣና ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በጥብቅ ደኑ ላይ ከፍተኛ የሆነ ህገ-ወጥ የደን ጭፍጨፋ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተው፣ “ጉዳዩን አስመልክቶ በተደረገ ጥናት ጭፍጨፋው በዚህ ፍጥነት ከቀጠለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ደኑ ሊጠፋ እንደሚችል” ታውቋል ብለዋል።

የወላይታ ዞን አካባቢ ጥበቃና ደን አየር ንብረት ለውጥ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘለቀ ዛራ በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ በሚገኙ ነባር ደኖች ላይ እየተፈጸመ ያለው ህገ-ወጥ ጭፍጨፋ አስከፊ እየሆነ በመምጣቱ ዘላቂ መፍትሄ መሰጠት የሚችል የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ ገብቷል።

በአሁኑ ወቀት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው በህገ ወጥ ደን ጭፍጨፋው ላይ የተሰማሩ አካላትን የመለየት ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በህገ-ወጥ መንገድ የፑንዱኒያ ደንን ሲጨፈጭፉ የተገኙ ስምንት ግለሰቦችና ግንዱን በመኪና ሲያጓጉዙ የነበሩ ሁለት ተሽከርካሪዎች መያዛቸውን ያስረዱት ኃላፊው፣ ግለሰቦቹ በአሁኑ ወቅት  ጉዳያቸው በፍርድ እየታየ መሆኑን አመልክተዋል።

ከ1 ሺህ 200 ሄክታር በላይ የሚሸፍነው የፑንዱኒያ የባህር ዛፍ ጥብቅ ደን ከ1972 እስከ 1976 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜያት ውስጥ የአፍሪካን ካርታ ቅርጽ እንዲይዝ ተደርጎ በህዝብና በመንግስት ተሳትፎ መተከሉን ከወላይታ ዞን አካባቢ ጥበቃና ደን አየር ንብረት ለውጥ ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም