አርበኞች ግንቦት ሰባት ለዲሞክራሲና ነጻነት በመታገል ለሀገራዊ ለውጡ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል...ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

60

ደብረ ማርቆስ የካቲት 11/2011 አርበኞች ግንቦት ሰባት በሀገሪቱ ዲሞክራሲና ነጻነት እንዲሰፍን ጭቆናን በመታገል አሁን ለተገኘው ለውጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል ሲሉ የንቅናቄው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

አርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ በምስራቅ ጎጃም ዞን ከሚገኙ አባሎቹና ደጋፊዎቹ ጋር በደብረማርቆስ ከተማ ትናንት ተወያይቷል።

በውይይቱ ላይ የንቅናቄው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሀኑ እንዳሉት አርበኞች ግንቦት ሰባት በሀገሪቱ ዲሞክራሲና ነጻነት እንዲሰፍን ታግሎ ያታገለ ድርጅት ነው።

በሃገር ውስጥና በውጭ ሀጋራት ሆኖ ባካሄደው ያልተቆጠበ ትግልም በአሁኑ ወቅት ለመጣው ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ የበኩሉን እገዛ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ንቅናቄው ሀገራዊ ለውጡን በመቀላቀል የተጀመረው ለውጥ እንዳይቀለበስ የዘር፣ የሃይማኖትና የጎሳ ልዩነት የሌለበት ትግል በማድረግ አንዲት ኢትዮጵያን ለመገንባት በተደራጀ መልኩ እየሰራ መሆኑንም ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡

"ባለፉት 27 ዓመታት በነበረው የጥቅም ፖለቲካ ተዘርቶ የነበረውን የእርስ በእርስ መከፋፈል ወደጎን በማለት ለውጡን ለመቀልበስ የሚደረገውን ሴራ በማስተዋልና በብልሃት ማክሸፍ ይገባል" ብለዋል።

አርበኞች ግንቦት ሰባት በሀገሪቱ የነበረውን ብሔርን ከብሔር የመከፋፈልና የአምባገነናዊ አገዛዝን በመቃወም ወደትግል ሲወጣ ሀገር ውስጥ በመሆን በግልጽና በስውር አላማውን ሲያስፈጽሙ ለነበሩ ግለሰቦችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የመድረኩ ዓላማ ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግና ከእዚህ በታቃራኒ አፍራሽ ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በተደራጀ አግባብ ለመመከት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ለቀጣይ አንድነትን ሊነጣጥል ከሚችል የዘር፣ የሃይማኖት እና የብሔር ፖለቲካ ነጻ የሆነ ትግልን ከማስቀጠል ባለፈ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አንድነት በመፍጠር ለመስራት ንቅናቄው በዝግጅት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

አባሎቻቸውም ከቀበሌ እስከዞን ድረስ ትክክለኛ የሀገራዊ አንድነት አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦችን ማደራጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በእለቱ የውይይቱ ተሳታፊዎች ሀገራዊ ለውጡ እስከታች አልወረደም ፣ ዞን ላይ ጥፋት የፈጸመ አመራር ክልል ላይ ሲሾም ይታያል፣ አሁንም ሙሰኝነት እና ዘረኝነት አለ ይህን እንዴት ማስተከካል ይችላል? ንቅናቄውስ ምን እየሰራ ነው? ለሚሉና መሰል ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ የንቅናቄው ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን በዞኑ ውስጥ የሚኖሩ ከ500 በላይ አባለት እና ደጋፊዎችም ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም