ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የደመቁበት የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች

106

አዲስ አበባ የካቲት 11/2011 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት በስፔን ሲቪያ በተካሄደው ማራቶን በሁለቱም ጾታዎች ድል ቀንቷቸዋል።

ኢትዮጵያውኑ አትሌቶች ከአንድ እስከ ስድስት ያለውን ደረጃ ይዘው ውድድሩን አጠናቀዋል።

በሴቶች ውድድር አትሌት ጉተኔ ሸኔ 2 ሰዓት ከ 24 ደቂቃ ከ 29 ሴኮንድ አሸናፊ ስትሆን በባለፈው ዓመት ውድድር በሞሮካዊቷ አትሌት ካውታር ቡላሊድ ተይዞ የነበረውን የቦታውን ክብረ ወስን በ 63 ሴኮንድ አሻሽላለች።

አትሌት አበባ ተክሉ 2 ሰዓት ከ 24 ደቂቃ ከ 53 ሴኮንድ በመግባት ሁለተኛ፤  አትሌት የኔነሽ ድንቄሳ ደግሞ 2 ሰአት ከ 24 ደቂቃ ከ 54 ሴኮንድ በማጠናቀቅ ሶስተኛ ወጥታለች።

አትሌት ሲፈን መላኩ፣ አትሌት ኡርጌ ዲሮና አትሌት አበሩ አያና በቅደም ተከተል ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

በወንዶች አትሌት ፅዳት አበጀ 2 ሰዓት ከ 6 ደቂቃ ከ 36 ሴኮንድ አሸናፊ ሲሆን እ.አ.አ በ 2017 በተካሄደው ውድድር ኬንያዊው አትሌት ታይተስ ኢኪሩ ይዞት የነበረውን የቦታውን ክብረወሰን በ 66 ሴኮንድ አሻሽሎታል።

አትሌት በላይ አሰፋ 2 ሰዓት ከ 6 ደቂቃ ከ 39 ሴኮንድ ሁለተኛ ሲወጣ አትሌት ብርሃኑ በቀለ 2 ሰዓት ከ 6 ደቂቃ ከ 41 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ውድድሩን ማጠናቀቁን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች የበላይነቱን በመያዝ የውድድሩ ድምቀት ሆነዋል።

ለ 35 ኛ ጊዜ በተካሄደው የሲቪያ ማራቶን በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።

በሌላ በኩል ከትናንት በስቲያ በእንግሊዝ በርሚንግሐም በተካሄደ  የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት ሳሙኤል ተፈራ 1 ሺህ 500 ሜትር ሩጫ ውድድር 3 ደቂቃ ከ 31 ሴኮንድ ከ 18 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት የርቀቱን የዓለም ክብረ ወሰን መስበሩ ይታወሳል።

አትሌት ሳሙኤል እ.አ.አ በ 1997 በሂቻም ኤል ጉሩዥ ተይዞ የነበረውን የርቀቱን ክብረ ወሰን በ 14 ማይክሮ ሴኮንድ በማሻሻል ከ 22 ዓመት በኋላ ክብረ ወሰኑን አስከብሯል። 

ከውድድሩ በፊት የርቀቱን ክብረ ወሰን ለመስበር እንደሚሮጥ ገልጾ የነበረው አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ  3 ደቂቃ ከ 31 ሴኮንድ ከ 58 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ በመውጣት በርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቱን አስመዝግቧል።

አውስትራሊያዊው አትሌት ስቲዋርት ማክስዌይን 3 ደቂቃ ከ 35 ሴኮንድ ከ 10 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

በበርሚንግሃሙ የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር በሴቶች የ 3 ሺህ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አልማዝ ሳሙኤል 8 ደቂቃ ከ 54 ሴኮንድ ከ 60 ማይክሮ ሴኮንድ አሸናፊ ሆናለች።

አትሌቷ ውድድሩን አሸንፋ በአጠቃላይ ድምር ውጤት የርቀቱ አሸናፊ በመሆን የ 20 ሺህ ዶላር ሽልማት ያገኘች ሲሆን እ.አ.አ 2020 በቻይና ናንጂንግ በሚካሄደው 18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ያለ ማጣሪያ መሳተፏንም አረጋግጣለች።

በውድድሩ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት አክሱማዊት አምባዬ 8 ደቂቃ ከ 54 ሴኮንድ ከ 97 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ ስትወጣ አትሌት መስከረም ማሞ  8 ደቂቃ ከ 55 ሴኮንድ ከ 8 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ ወጥታለች።

በውድድሩ አትሌት እጅጋየሁ ታዬና ሀዊ ፈይሳ በቅደም ተከተል 4ኛ እና 6ኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

ጥር 18 ቀን 2011 ዓ.ም በአሜሪካ ቦስተን ከተማ የተጀመረው የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር ከነገ በስቲያ በጀርመን ዱሲልዶርፍ ከተማ በሚካሄደው ውድድር ፍጻሜውን ያገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም