ቀዳማዊት እመቤት በጅግጅጋ ከተማ በ20 ሚሊዮን ብር ወጪ ለሚገነባው የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ

177

ጅግጅጋ የካቲት 11/2011 ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በ20 ሚሊዮን ብር ወጪ ለሚገነባው  ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ።

በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በሚመደብ በጀት የሚገነባውና 'አመንጂን ዩጎል' የተሰኘው ትምህርት ቤት በአንድ ዓመት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል ተብሎ ይጠበቃል። 

የተለያዩ ክልሎች ተማሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያሉበት ቦታ ሩቅ በመሆኑ ቀጣይ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ይገደዳሉ።

ይህ ትምህርት ቤትም በአካባቢው ያለውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እጥረት በማቃለል ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ቁጥር ለመቀነስ እንደሆነም ወይዘሮ ዝናሽ በዚሁ ወቅት ተናግረዋል።

የትምህርት ቤቱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደርና የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ርብርብ እንዲያደርጉ ወይዘሮ ዝናሽ ጠይቀዋል።

ተመሳሳይ ችግር ባለባቸው የተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን አመቺ በሆኑ ቦታዎች ላይ የማስፋፋት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ወይዘሮ ዝናሽ ገልጸዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፋ ኡመር በበኩላቸው በክልሉ 186 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቢገኙም ደረጃውን ያሟሉት በጅግጅጋና በቀብሪደሃር የሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸውን ያነሳሉ።

አዲስ የሚገነባው ይህ ትምህርት ቤት ደረጃቸውን ያሟሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤቶችን ቁጥር ወደ ሶስት ያሳድገዋል ብለዋል።

ከወራት በፊት ከፍተኛ የሰላም እጦት ይወራበት በነበረው የሶማሌ ክልል ዛሬ ሰላም ሰፍኖ ስለትምህርት መወራት መጀመሩ መልካም የሚባል ነገር እንደሆነም አቶ ሙስጠፋ አንስተዋል።

የትምህር ቤቱ መገንባት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ በማድረግ ብቁ ዜጋን ለመፍጠረ ከማስቻል ባሻገር በክልሉ ያለውን አጠቃላይ የትምህርት ተደራሽነት ለማሳደግ ጠቃሚ እንደሆነም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም