ለኤርትራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲና የባህል ልዑክ በአዳማ ከተማ አቀባበል ተደረገለት

81

አዳማ የካቲት 11/2011 ለኤርትራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲና የባህል ልዑክ በአዳማ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደረገለት።

ለልኡኩ  ትናንት ማምሻውን በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶችና በአባ ገዳ አዳራሽ በተዘጋጀው ደማቅ የአቀባበል ስነ ሥርዓት ላይ የአዳማ ከተማ አስተዳደር አካላት፣ አባ ገዳዎችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ገረመው ሁሉቃ እንዳሉት የባህል ቡድኑ መገኘት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተጀመረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያጎለብታል።

የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች እርስ በርስ ካላቸው የጠበቀ ቁርኝት በተጨማሪ ከጨቋኝ ሥርዓት ለመላቀቅ በጋራ ያደረጉት ትግል ያስተሳስራቸዋል ያሉት ዶክተር ገረመው የኦሮሞ ህዝብ ለኤርትራ ሉአላዊነት ክብር እንዳለው ተናግረዋል።

"የኦሮሞ ምልክት የሆነው የገዳ ሥርዓት ጠበቃ ናቸው ብለን የምንወስዳቸው ፕሮፌሰር አስምሮም ለገሰ ከኤርትራ ምድር የበቀሉ ምሁር በመሆናቸው ለባህል ቡድኑ ላቅ ያለ ክብር አለን" ብለዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከድር መሐመድ በበኩላቸው በደም የተሳሰሩ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ለሁለት አስርት ዓመታት በጥቂት ግለሰቦች ፍላጎትና ተግባር ተራርቀውና ተለያይተው እንደነበር አስታውሰዋል።

"በአሁኑ ወቅት የሁለቱ ሀገራት መሪዎችና ህዝቦች ባሳዩት ቁርጠኝነት የተለያዩበት ግንብ ፈርሶ የዛሬው ቀን እውን መሆን ችሏል" ሲሉ ገልጸዋል።

"የኦሮሞ ህዝብ የጥንት እኩልነት ሥርዓት አባት ነው" ያሉት ደግሞ የኤርትራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲና የባህል ልኡክ  ቡድን መሪ አቶ ሚካኤል ተፈሪ  ናቸው።

"የኤርትራን ህዝብ የወዳጅነት ሰላምታና የመልካም ምኞት ለማብሰር በመካከላችሁ ተገኝተናል" ያሉት አቶ ሚካኤል የጦርነትና የመራራቅ ዘመን ተሽሮ በምትኩ የሰላም፣ የእርጋታና የመልካም ጉርብትና ዘመን መንገሱን አመልክተዋል።

የኤርትራ ባህል ቡድን ትናንት ምሽት በአባገዳ አዳራሽ የተለያዩ ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃዎችን በማቅረብ ታዳሚውን አዝናንቷል። 

63 አባላትን ያካተተው የኤርትራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲና የባህል ቡድን ዛሬ የኦሮሞ ሰማዕታት ኃውልትና የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክን ይጎበኛል ተብሎ ይጠበቃል።

ቡድኑ ከአዳማ ቆይታው በኋላ ነገ ወደ ሀዋሳ ከተማ የሚያቀና ሲሆን የካቲት 14 ቀን 2011 ዓ.ም ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ ዝግጅቱን ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም