በደሴ ከተማ የተገነባው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተመረቀ

1062

ደሴ የካቲት 10/2011 በደሴ ከተማ  በ29 ሚሊዮን 600 ሺህ ብር  ወጪ የተገነባው  ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ዛሬ ተመረቀ፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በምረቃ ስነስርዓቱ ወቅት እንዳሉት ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች ተወዳዳሪና ተመራማሪ ሆነው እንዲወጡ ልዩ ድጋፍና ክትትል ያደርጋል፡፡

በክልሉ የመጀመሪያ የሆነውን ትምህርት ቤቱ  በመደገፍና በመከታተል ተማሪዎች ለክልሉና  ለኢትዮጵያ ህዝብ ችግር ፈች ጥናትና ምርምር መስራት እንዲችሉ መንግስት የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡

የግንባታውን ሙሉ ወጭ ለሸፈኑት ለክልሉ ተወላጅ  ኢንጂነር ጸደቀ ይሁኔ ርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ተማሪዎች ለፍሬ እንዲበቁና የትምህርት ቤቱ ዓላማም እንዲሳካ ሁሉም ድጋፍና ክትትል በማድረግ የድርሻዉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፍያለ በበኩላቸው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራቱን ለማረጋገጥ፤ በቁና ተወዳዳሪ ምህራንን ለማፍራት ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡ 

ይህንን ለማስፋፋት በታያዘው ዓመት  ከ200 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ  ወጪ በደብረብርሃን ከተማ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ መጀመሩን አመልክተው በቀጣይ በባህርዳርና በጎንደር ለመስራት መታቀዱን ጠቅሰዋል፡፡

በደሴ በተገነባው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ከሁሉም የክልሉ ዞኖች የተወጣጡና በ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያመጡ  ተማሪዎች ከሳምንት በፊት ወደ ትምህርት ቤቱ ገብተው እንዲማሩ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

በአልማ፣ በወሎ ዩኒቨርሲቲና በክልሉ መንግስትት በተገኘ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የውስጥ ቁሳቁስ ተማልቶለት ትምህርት ከጀመሩት 125ተማሪዎች መካከል 26 ሴቶች መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የትምህርት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በለጠ ኃይሌ ናቸው፡፡

ለአገልግሎት የበቃው የትምህርት ቤቱ ግንባታ የተጀመረው በ2006 ዓ.ም. ሲሆን በውስጡ  መማሪያ ፣ ቤተ ሙከራ፣ ቤተ-መጽሐፍት ፣ መመገቢያ አዳራሽ፣ የተማሪዎችን ማደሪያና ሌሎችንም መገልገያ ክፍሎችን አካቶ 13 ህንጻዎች  እንዳሉት ተመልክቷል፡፡

ትምህርት ቤቱን ያስገነቡት ኢንጅነር ጸደቀ ይሁኔ ትምህርት የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች  ለማበረታታትና አባታቸውን ለማስታወስ ያደረጉት ድጋፍ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡