የማዕከላዊና ምእራብ ጎንደር ዞኖችን ሰላም ለማስጠበቅ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

2090

ጎንደር የካቲት 10/2011 በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በጸረ-ሰላም ኃይሎች የደረሰው የዜጎች ሞትና መፈናቀል በማያዳግም ሁኔታ ለማስቆም እየሰሩ መሆናቸውን የመከላከያ ሰራዊት 33ኛ ክፍለ ጦርና  የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቁ።

የክፍለ ጦሩ ዋና አዛዥና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በጋራ በጎንደርና አካባቢው ወቅታዊ  የጸጥታ ሁኔታ ላይ ዛሬ በጎንደር ከተማ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም የአካባቢው ሰላም ወደ ነበረበት እስኪመለስ ድረስም ከጎንደር መተማ እና ከጎንደር ሁመራ በሚወስደው መንገድ በ5 ኪሎ ሜትር ርቀት በቡድንም ሆነ በተናጥል ትጥቅ ይዞ የመንቀሳቀስ ክልከላ ተደርጓል ፡፡  

ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም በሰጡት መግለጫ በህዝቦች መስዋእትነት የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስና አካባቢውን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ የታጠቁ ሃይሎች ሰላምን ለማደፍረስ ብርቱ መፍጨርጨር ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የዜጎች ሞት መፈናቀልና ከፍተኛ የንብረት ውድመት መከሰቱን ኮሚሽነሩ ገልጸው ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦች መጽናናትን በክልሉ መንግስት ስም ተመኝተዋል።

የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ከመፍታት አኳያም የፌደራልና የክልሉ የጸጥታ ሃይል አካባቢውን ወደ ነበረበት ሁኔታ ለመመለስ በፌደራልና በክልሉ መንግስት ትእዛዝ መሰጠቱን በመግለጫቸው አመልክተዋል።

“የጸጥታ ሃይሎቹ በጋራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማያዳግም ሁኔታ የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ርብርርብ ያደርጋሉ” ብለዋል።

አካባቢውን ሲያተራምሱ የነበሩ ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ለዜጎች ሞት መፈናቀልና ለንብረት ውድመት ምክንያት የሆኑ ሃይሎች በቁጥጥር ስር የሚውሉበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

በአካባቢው አስተማማኝ የሆነ የህግ ማስከበር ስራ እንደሚሰራ የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ህብረተሰቡ ይህን ተገንዝቦ የጸጥታ ሃይሉ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ተሳታፊና ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ይህን ህግ የማስከበር ተልእኮ ለማስፈጸምና በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም እስኪረጋገጥና በቀጠናው ሰዎች ህይወታቸውን የሚያጡበት ሁኔታ እስኪቆም ድረስ በጎንደርና አካባቢው ጊዚያዊ ክልከላዎች ተላልፈዋል።

በዚህም መሰረት ከጎንደር መተማ እና ከጎንደር ሁመራ መስመር በግራና በቀኝ በ5 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ በቡድንም ሆነ በተናጥል ትጥቅ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።

በጎንደር ከተማም ሰላማዊ የፖለቲካ የኢኮኖሚና የቱሪዝም እንቅስቃሴውን የሚገድቡ ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩም ከተፈቀደለት የጸጥታ ሃይል ውጪ ማንኛውም ሃይል ትጥቅ ይዞ እንዳይንቀሳቀስ ተከልክሏል።

ክልከላ በተደረገባቸው አካባቢዎች ትጥቅ ይዞ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ሃይል መንግስትና ተልእኮ በተሰጠው የመከላከያ ሰራዊትና የክልሉ የጸጥታ ሃይል ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

ሌሎች ለጸጥታ ስራ አጋዥ እንሆናለን ብለው የሚያስቡ ሃይሎች በመንግስት በኩል ፈቃድና ስምሪት እስኪሰጣቸው ድረስ በየትኛውም የጸጥታ ማስከበር ተልእኮ መሰማራት የተከለከለ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

የ33ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል አለሙ አየነ በበኩላቸው “የዜጎች ህይወት ከዚህ በኋላ በከንቱ እንዲያልፍ አንፈቅድም ተመጣጣኝ እርምጃ በመውሰድ የአካባቢው ሰላም ወደ ነበረበት እንዲመለስ ይደረጋል” ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የፌደራል መከላከያ ሰራዊት ወደ ክልሉ ገብቶ የፀጥታ ስራ እንዲሰራ ትእዛዝ መሰጠቱን ጠቁመው ህዝቡ ከጸጥታ ሃይሉ ጎን በመሆን የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በአካባቢው ላይ የተላለፉትን ክልከላዎች ህዝቡና በሰላማዊ መንገድ የታጠቁ ሃይሎች በማክበር ለተግባራዊነቱ እንዲረባረቡም አሳስበዋል።