የግብር አሰባሰቡን ውጤታማ ለማድረግ የግብር ከፋዮች መረጃ እያያዝ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል

68

አዲስ አበባ  የካቲት 10/2011  በአገሪቷ ያለውን የግብር አሰባሰብ ውጤታማ ለማድረግ የግብር ከፋይ መረጃ እያያዝና ተደራሽነት ላይ መንግስት ትኩረት አድርጎ መስራት እንዳለበት ተጠቆመ። 

አሁን በአገሪቷ እየተስተዋለ ያለውን ዝቅተኛ የግብር አሰባሰብ ስርአት ለማሻሻል በመንግስት በኩል የተለያዩ ተግባራቶች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተገኙበት የግብር ንቅናቄ በይፋ ተጀምሮ ለአንድ ዓመት እንዲዘልቅ የተለያዩ ኩነቶች በተያዘላቸው ጊዜ እየተካሄዱም ነው።

የንቅናቄው አካል የሆነው የ5 ኪሎ ሜትር ሩጫም ''ግዴታዬን እወጣለሁ መብቴን እጠይቃለሁ'' በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ  መስቀል አደባባይ ተካሂዷል። 

በውድድሩ ላይ ከተገኙት መካከል ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ተሳታፊዎች እንዳሉት መንግሥት በተለይ ግብርን በሚመለከት የመረጃ አያያዝና ተደራሽነት ላይ ክፍተት ይስተዋልበታል። 

ወጣት ዘላለም አባተ እንደሚለው ግብር በሚፈለገው መጠን እንዳይሰበሰብ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ዋናው በሚመለከተው አካል ስለ ግብር ከፋዩ የተሟላ መረጃ አለመያዙ ነው።       

''ማን ምን ያንቀሳቅሳል?፣ ምን ሸጠ? ምን ያክል ገቢ በምን ያህል ግዜ አገኘ የሚሉ ጉዳዮችን በአግባቡ ለይቶ የመዘያዝ ችግር አለ'' ያለው ወጣት ዘላለም ይህም ታክስ በግምት እንዲጣል ያደርጋል ባይ ነው።     

ለዚህ ደግሞ መፍትሄው ግብር ሰብሳቢው ተቋም የግብር ከፋዩን የስራ ሁኔታ በአግባቡ ተከታትሎ መረጃ መያዝ ይጠበቅበታል ብሏል።

ትላልቅ ቢዝነስ የሚያንቀሳቅሱ ነገር ግን ግብር የሚሰውሩ አካለት መኖራቸውን የጠቆመው ወጣቱ ይህንን ችግር ለመፍታት ደግሞ የማስተማርና ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ነው ያለው።

የኀብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግም መሰል የንቅናቄ መርሃ ግብሮች ፋይዳቸው የጎላ በመሆኑ በስፋት ሊሰራበት ይገባል የሚል አስተያተም ሰጥቷል። 

ሌላዋ የሩጫው ተሳታፊ ብዙነሽ በቀለ በበኩሏ ከአሁን በፊት ገቢን ታሳቢ ያላደረገ ግብር እንደሚጣል አንስታ በቀጣይ ከአቅም በታችም ከአቅም በላይም ግብር ላለማስከፈል መንግሥት አሰራር ማበጀት አለበት ብላለች። 

ኀብረተሰቡ ግብር መክፈልን እንደ ግዴታ ይቆጥራል፤ መጠየቅን ግን እንደ መብት አይቆጥርም ያለው ደግሞ ወጣት ግርማ ቡልቻ ነው።

እንደ ወጣቱ ገለፃ ግብር ከፋዩ "የከፈልኩት ግብር የት ደረሰ? ምን ላይ ዋለ?" የሚለውን ባህል ሊያዳብር ይገባል።   

በኢትዮጵያ ግብር አሰባሰቡ ከአገራዊ ምርት አንጻር ሲታይ በተለይ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እየቀነሰ መምጣቱን የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።  

በመረጃው መሰረት በ2007 ዓ.ም 13 ነጥብ 4 በመቶ የነበረው የግብር አሰባሰብ እያሽቆለቆለ መጥቶ ባለፈው ዓመት 10 ነጥብ 7 በመቶ ደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም