ባለስልጣኑ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማሳለጥ በዘጠኝ ሚሊዮን ብር ወጪ አውቶሜሽን ፕሮጀክት እየተገበረ ነው

124

አዳማ የካቲት 10/2011 የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን የትራንስፖርት ዘርፉን ለማሳለጥ በዘጠኝ ሚሊዮን ብር ወጪ አውቶሜሽን ፕሮጀክት ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታወቀ።

የፕሮጀክቱ አካል የሆነው የምስራቅ ሸዋ ዞን ቅርንጫፍ ዋና ዋና አገልግሎት አውቶሜሽን ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።

የባለስልጣኑ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሙሌ ደሳለኝ እንዳስታወቁት በክልሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የተቀላጠፈ አገልግሎት የሚሰጥ ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

ፕሮጀክቱ በሙከራ ደረጃ በተመረጡ ምስራቅ ሸዋና ወለጋ ዞኖች እንዲሁም በሻሸመኔ፣ቡራዩና ሰበታ ከተሞች በሚገኙ ትራንስፖርት ጽህፈት ቤቶች ትግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ወደ ዞኖችና ከተሞች ለማስፋፋት መታቀዱን ምክትል ኃላፊዋ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የመረጃ ሥርዓት በመዘርጋት የመኪና ምዝገባ፣ምርመራና የፋይል ዝውውርን፣የአዲስ ተሽከርካሪ ምዝገባና የባለንብረት ስም ዝውውር ይከናወንበታል።

እንዲሁም የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ፣ የትራንስፖርት እንቅስቃሴና ሌሎች አገልግሎት በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓት  መዘርጋት ያስችላል ብለዋል።   

የዳፍቴክ ሶሻል ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሶሻል በየነ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ኋላ ቀርና የተንዛዛ አስራርን በማስቀረት አሰራሮችን ለማዘመንና በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

ሌላኛው የመረጃ  አያያዝ ሥርዓት በመዘርጋት በመዝገብ ቤት ያለውን የተዝረከረከ አሰራርና አደረጃጀት ለማስተካከልና መረጃ ወደ አንድ ቋት በማስገባት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለተጠቃሚዎች እንደሚያደርስ አስረድተዋል።

በተለይ የመንጃ ፍቃድ አሰጣጥንና ሂደትን ከሰው ንኪኪ ነፃ ለማድረግ አውቶሜሽን ፕሮጀክቱ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በምስራቅ ሸዋ ዞን በፓይለት ደረጃ በተካሄደው ፕሮጀክት 78 ሺህ የአሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪዎች ፋይልን ዲጂታላይዝ በማድረግና ሲስተም ውስጥ በማስገባት መጪው ሣምንት የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቁመዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የትራንስፖርት አገልግሎትን ማዘመን፣ የተፋጠነ፣ጥራት ያለውና ከሌብነት የፀዳ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ስለሚያደርግ እንዲስፋፋ አሳስበዋል።

የሪል ስቴት ንግድና ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭ አቶ ሰኢድ አህመድኑር ለምስራቅ ሸዋ ዞን ትራንስፖርት ባለስልጣን በ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ዘመናዊ ህንፃ በማስገንባት ፕሮጀክቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸው በዕለቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም