በተሰማሩበት ስራ በቂ ድጋፍ ባለማግኘታቸው መቸገራቸውን የመቱና ጎሬ ከተማ ወጣቶች ገለጹ

59

መቱ የካቲት 9/2011 የስራ ቦታ ጥበት ፣ የብድር አቅርቦትና የገበያ ችግር በስራቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸው በኢሉአባቦር ዞን ኢዜኣ ያነጋገራቸው የመቱና የጎሬ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።

በጎሬ  ከተማ ከሌሎች አምስት ጓደኞቿ ጋር በዶሮ እርባታ የተሰማራቸው ወጣት ሰአዳ ሁሴን በሰጠችው አስተያየት ለዶሮ እርባታ ተብሎ የተሰጣቸው ስፍራ ጠባብ  በመሆኑ ስራቸውን በአግባቡ ለማከናወን ተቸግረዋል።

በተለይ “ከዶሮ ቤቶች የሚወጣውን ቆሻሻ የምናስወግድበት ቦታ የለንም” የምትለው ሰአዳ በዚህም ምክንያት ለወጪ እየተዳረጉ መሆናቸውን ተናግራለች።

ለመነሻ ካፒታል ከጠየቁት 100 ሺህ ብድር ውስጥ የተፈቀደላቸው ግማሽ ያህሉ ብቻ ስለሆነም ስራቸውን ለማስፋፋት እንቅፋት እንደሆነባቸው ጠቁማለች።

በመቱ ከተማ በእንጨትና ብረታ ብረት ስራ የተደራጀ ወጣት አምባቸው ታደሰ እንደገለጸው ለምርታቸው በቂ የገበያ ትስስር ስላልተፈጠረላቸው በእንቅስቃሴያቸው ውጤታማ መሆን አልቻሉም።

 “የመንግስት ተቋማት ጨረታ ሲያወጡ የብረት ስራ ነጥለው አያወጡም ሁሉንም ፍላጎት አንድ ላይ ያወጣሉ” ያለው ወጣቱ በዚህም  ቅድሚያ አግኝተው ምርት ማቅረብ አንዳልቻሉ አስረድቷል።

የኢሉአባቦር ዞን የስራ እድል ፈጠራና ከተማ ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዮት ለገሰ በበኩላቸው በእንጨትና ብረታ ብረት መስክ የተሰማሩ ማህበራት በተለየ ሁኔታ ተወዳድረው  ምርታችውን ለመንግስት ተቋማት የማቅረብ ችግር እንደነበረ ገልጸዋል፡፡

“በዚህ አመት ይሄንን ችግር የቀረፈ አዲስ መመሪያ በመዘጋጀቱ የገበያ ትስስር ይፈጠራል” ብለዋል።

በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከተሰራጨው የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር ውስጥ  ከ92 ከመቶ በላይ የሚሆነው በወቅቱ ባለመመለሱ ተጨማሪ ብድር ለማቅረብ እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

የወጣቶችን የመስሪያ ቦታ ችግር ለመፍታትም በዚህ አመት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት በመቱ ከተማ ያለ አግባብ በግለሰቦች የተያዙ 20 የመንግስት ቤቶችን በማስለቀቅ በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች መተላለፋቸውን ጠቁመዋል።

እንደ ኃላፊው ገለፃ በመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት በዞኑ በአንድ ሺህ 148 ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ  ከዘጠኝ ሺህ የሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል።

ውጤታማ እንዲሆኑም ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር የተሰራጨ ሲሆን 144 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር እንደተፈጠረም ከዞኑ የስራ እድል ፈጠራና ከተማ ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት የተገኘው መኘረጃ ያመለክታል።

እስከ በጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ ድረስም ከ32 ሺህ የሚበልጡ የገጠርና የከተማ ወጣቶችን በተለያዩ የገቢ ማስገኛ መስኮች ለማሰማራት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም