የአምቦ ዩኒቨርሲቲ አረምን ለእንስሳት መኖነት ጥቅም ላይ አዋለ

994

የካቲት 9/2011የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ”ዳክዬ” የተባለ አረምን በምርምር አውጥቶ  ለእንስሳት መኖነት  ጥቅም ላይ ማዋሉን አስታወቀ፡፡

ተቋሙ በተጨማሪም አትክልትን የሚያጠቃ ተባይን  ለመከላከል ለአርሶ አደሩ ድጋፍ እየሰጠ ነው፡፡ 

ዩኒቨርስቲው በግብርና ፣ በጤና ፣ በአካባቢ ጥበቃና በሌሎችም ዘርፎች ከ100 በላይ ችግር ፈቺ  የምርምር ፕሮጀክቶች አሉት፡፡

ከነዚህ ውስጥ  በተለይ ”ዳክዬ” የተባለ አረምን ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት ጋር በመተባበር ላለፉት ሶስት ዓመታት ባደረገው ምርምር ውጤታማ መሆናቸውን በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር ብዙነሽ ሚዴቅሳ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

በምርምር የተገኘው አረም ለመኖነት የሚውለው በመጠለያ ውስጥ ውሃ በተጨመረባቸው ገንዳዎች በማባዛት በማከናወን ከሌላ የእንስሳት ጋር 20 በመቶው ያህሉ በማደባለቅ ነው፡፡

ገንቢ የሆኑ ንጥረ ነገሮቹን በመያዙ በአሁኑ ወቅት ለወተት ላሞች፣ እንቁላልና ለስጋ ዶሮዎች መኖ በማዋል ውጤታማ መሆናቸውን  ዶክተር ብዙነሽ አስረድተዋል፡፡

እስካሁንም መኖውን የሚጠቀሙ ዶሮዎች እንቁላላቸው ከውጭ ዝርያዎች የተለየ፣ የአስኳሉ ቀለም ቢጫና መጠኑም ከፍ ያለ እንዲሁም የወተት ላሞችን ለሰባት ወራት ያህል ምርት ለመስጠትበ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

በቀላሉ የሚዘጋጅ በመሆኑ ለእንስሳት መኖ የሚወጣውን ወጪ የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ ምርታማነትንም እንደሚጨመር አመልክተው፣  ስለአጠቃቀሙ  በማህበር ለተደራጁ ሴቶች ስልጠና ሰጥተው እየተሰራበት መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል፡፡

አትክልትና ሌላውን አዝርዕት የሚያጠቃ ተባይን ለመከላከል ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከውጭ የሚገቡ ኬሚካሎችን ውጤታማነታቸውን በመስክ ሙከራ ተረጋግጦ ሥራ ላይ እንዲውሉ መደረጉንና ለአርሶ አደሩም ድጋፍ እየሰጡ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

ዶክተር ታደሰ ሽብሩ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪና መምህር ናቸው። በተባይ ምክንያት በተለይ በሽንኩርት፣ ጥቅል ጎመንና ቲማቲም ላይ የሚደርሰው ተጽዕኖ ለመከላከል ለአርሶ አደሩ የመድኃኒት አቅርቦትና የምክር አገልግሎት በነጻ በመስጠት እያገዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ውጤታማ በመሆን አገልግሎቱን ለማስፋፋት ጥረት እያደረጉ ናቸው፡፡

የዩኒቨርስቲው ባለሙያዎች ባደረጉላቸው ድጋፍ ተባይ በአትክልታቸው ላይ ያደርስባቸው የነበረው አሁን መቃለሉን የተናገሩት ደግሞ በምዕራብ ሸዋ ዞን ቶኬ ኩታዬ ወረዳ የደጋ ፍሌ ቀበሌ አርሶ አደር እሸቱ ለሚ ናቸው፡፡

በአምቦ ከተማ የቀበሌ ሁለት ነዋሪ ወይዘሮ ትዕግስት አበበ በበኩላቸው ከ11 ሴቶች ጋር ተደራጅተው ዩኒቨርሲቲው ባመቻቸላቸው የመኖና የስልጠና ድጋፍ በዶሮ እርባታ ላይ በመሰማራት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይ የዶሮዎቹ እንቁላል ከሽያጭ አልፎ ለልጆቻቸው ምግብነት በማዋል ተጠቃሚ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

የአምቦ ዩኒቨርስቲ በቀጣይነትም የምርምር ውጤቶችን ለሁሉም የአካባቢው ወረዳዎች ለማዳረስ ሥራውን እንደሚያጠናክር አመልክቷል፡፡