አገር በቀል ማህበራዊ እሴቶችን ለማበልፀግ በትምህርት ስርዓት ውስጥ ማካተት ይገባል

148

አዲስ አበባ የካቲት 9/2011በኢትዮጵያ እየተሸረሸሩ የመጡትን አገራዊ እሴቶችን ለማበልፀግ በትምህርት ስርዓት ውስጥ አካቶ ማስተማር እንደሚገባ ምሁራን ገለፁ።

የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራኑ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እሴቶቹ በአገሪቱ እየተወሰደ ያለውን የለውጥ እርምጃ ሊያግዝ በሚችልበት መልኩ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

እሴቶቹን ለማጠናከርም የአስተዳደራዊና ፖሊቲካዊ ርዕዮተ ዓለሞችን ከባዕድ አገሮች ከማምጣት ይልቅ የአገር በቀል ዕውቀቱን ከሳይንሱ ጋር በማስታረቅ ተስማሚውን መቅረፅ አስፈላጊ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

በአገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግጭቶችና አለመግባባቶች ተበራክተው በየክልሉ ዜጎችን ከቀዬአቸው እያፈናቀለ ያለውን ችግር ለመፍታት አገራዊ እሴቶቹ ጠቃሚ በመሆናቸው ሊጠናከሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በኀብረተሰቡ መካከል የነበሩ የመተሳሰብና አብሮ የመኖር ማህበራዊ እሴቶች በመሸርሸራቸውና በመዳከማቸው የችግር መፍቻ መሳሪያ በመሆን እያገለገሉ እንዳልሆነም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጠና ደዎ ''አሁን ካለው አኗኗራችን መረዳት እንደሚቻለው ማህበራዊ እሴቶቻችን እየተዳከሙና እየተሸረሸሩ መምጣታቸውን ነው" ብለዋል።

"የመረዳዳት፣ የመከባበር፣ አብሮ የመኖርና የመሳሰሉት አገር በቀል አቅማችን እየተዳከመ መምጣት የማህበራዊ እሴቶቻችን እየተዳከሙ እንጂ እየተጠናከሩ መምጣታቸውን አያሳዩም" ያሉት ዶክተር ጠና፤ ለአገር በቀል እሴቶች ተገቢው ዋጋ መሰጠት እንደሚገባው ያስገነዝባሉ።

ከውጭ የተዋስናቸው ዓለም አቀፍ እሴቶችና አገር በቀል እሴቶቻችን ተደባልቀው በጥቅም ላይ እየዋሉ መሆናቸውንም በቀላሉ ማስተዋል እንደሚቻል ነው ዶክተር ጠና የሚናገሩት።

አገር በቀል እሴቶችን በማደራጀት ጥቅም ላይ ማዋል አለመቻሉ ጉዳት እንዳለው የገለጹት ዶክተር ጠና፤ ከውጭ የሚመጡ እሴቶች ለአገሪቱ በሚሆን መልኩ ተቀምረው አለመወሰዳቸው ለተለያዩ ችግሮች መንስኤ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተውሶ የሚመጡ ርዕዮተ ዓለሞች ከህዝቡ ባህል ጋር ካልተቃኘና በአግባቡ ግንዛቤ አግኝቶ ካልተተገበረ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን ገልጸው የህይወት መርህ የሆኑ አገራዊ እሴቶች በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ መካተት እንዳለባቸው ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

"የአገረሰብ አስተዳደር፣ የህግና ፍትሕ ስርዓቶች በኢትዮጵያ" የሚል መፅሀፍ አዘጋጅተው ያቀረቡት አቶ አብዱልፈታ አብደላ በበኩላቸው የሁሉም ተግባራት መሰረት የነበሩት ማህበራዊ እሴቶች ከውጭ በመጡ እሴቶች የተነሳ "ግብዓተ መሬታቸው እየተፈፀመ" ነው በማለት ይገልጻሉ።

የጥንታዊ ስርዓተ መንግስት ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በአገር በቀል እሴት በተመራችባቸው ዘመናት በስልጣኔ ተወዳዳሪ እንደነበረችና ያ ዘመን አገሪቷ ዓለም የመዘገበላትን ታላላቅ ስራዎች ማከናወኗን ተናግረዋል።

በአገር በቀል እውቀትና እሴት መመራት ከቀረ በኋላ ወደ ማሽቆልቆል፣ ግጭትና አለመግባባት እንዲሁም አለመግባባቶችን ወዳለመቆጣጠር ችግር እየተገባ እንደሆነ ተናግረዋል።

ስለዚህ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የትምህርት የፍትህና የመንግስት ርዕዮተ ዓለማችንን በራስ ቅኝት መቀመር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ለአገር የሚያስፈልጉ አለም አቀፍም ሆነ አገር አቀፍ እሴቶችን ለመለየት የውይይት መድረክ ሊኖር እንደሚገባም ምሁራኑ ተናግረዋል።

እሴቶችን የሚያጎለብት ተቋማዊ አደረጃጀት እንደሚያስፈልግ የገለፁት ምሁራኑ በተለያየ የአገሪቷ አካባቢዎች ያሉ እሴቶችን በማጥናት ሁሉም የሚግባባበት እሴት ማጎልበት እንደሚገባም ገልፀዋል።

ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያግባባ እሴታዊ ስርዓት (ቫልዩ ሲስተም) ሊፈጠር ይገባልም ብለዋል ምሁራኑ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም