ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች በጊዜ አለመጠናቀቅ የሀገሪቱን የእድገት ጉዞ እየገታው ነው... የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

48

መቀሌ የካቲት 9/2011የመንግስት ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ አለመጠናቀቅ ሀገሪቱን ከድህነት ለማውጣት የተጀመረውን እንቅስቃሴ እየገታው መሆኑን ሁለት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ገለጹ፡፡

ምሁራኖቹ እንዳሉት ተጠያቂነትና ግልጽነት ያለው የአሰራር ስርአትን መዘርጋት የፕሮጀክቶቹን አፈጻጸም ከማሻሻል ባለፈ ህዝቡ በመንግስትና በፕሮጀክቶቹ ላይ የሚኖረውን እምነት እንያዲጎለብት ያደርጋል፡፡

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁር ዶክተር ኪዳነማሪያም ገብረእግዚአብሔር ለኢዜአ እንዳሉት መንግስት ባለፉት ዓመታት የጀመራቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የተለጠጡ ናቸው።

በፍጥነት ከድህነት ለመውጣት ካለ ፍላጎት የመነጨ የስኳር፣ የማዳበሪያ፣ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በአንድ ጊዜ ቢጀመሩም ፕሮጀክቶቹን በተለያዩ ምክንያቶች በአንድ ጊዜ ማጠናቀቅ አልተቻለም።

የፕሮጀክቱ መጀመር በአዎንታ የሚታይ ቢሆንም በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቃቸው ሀገሪቱን ከድህነት ለማውጣት የተጀመረውን እንቅስቃሴ እየገታ መሆኑን ገልጸዋል።

የፕሮጀክቶቹ መጓተት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን መጨረሻ ለማሳካት የተያዘው ግብ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑንም ጠቁመዋል።

" ከፕሮጀክቶቹ ሊገኙ የሚችሉ ማህበራዊና ኦኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ሀገሪቱ እንድታጣ ከማድረግ ባለፈ የሥራ አጥ ቁጥር እንዲጨምርም አድርጓል" ብለዋል፡፡

ዶክተር ኪዳነማርያም እንዳሉት በተለይ የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ በሚወጡ ሪፖርቶች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ህዝቡ ለግድቡ ባለው መነሳሳት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው፡፡

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁም በመንግስት በኩል ግልጽነት ያለው የአሰራር ሥርአት በመዘርጋት ክትትል ሊደረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

አሁን እየታየ ያለውን የፕሮጀክቶች መጓተት ለማስቀረት ተገቢ ክትትልና ቁጥጥር ከማድረግ ባለፈ የፕሮጀክቶቹ ኃላፊዎችን በትምህርት ዝግጁነታቸውና በብቃታቸው እንዲመደቡ ማድረግ እንደሚገባ ዶክተር ኪዳነማሪያም ገልጸዋል፡፡

የሜጋ ፕሮጀክቶቹ የሥራ አፈጻጸምና የገንዘብ አጠቃቀም በየጊዜው ለህዝብ ግልጽ ከተደረገ ህዝቡ በመንግስትና በልማት ፕሮጀክቶቹ ላይ ያለው አመኔታ እየጎለበተ እንደሚመጣም ዶክተር ኪዳነማሪያም ተናግረዋል፡፡

" የሜጋ ፕሮጀክቶች መጓተት በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የሥራ አፈጻጸም ነጸብራቅ ነው " ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የዴቨሎፕመንት ጥናት ምሁር ዶክተር ቢሆን ካሳ ናቸው፡፡

የባለ ድርሻ አካላት ያለ መናበብ ችግርም  ለመጓተቱ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመው ይህም  መንገድን ጨምሮ በሌሎች አነስተኛ ፕሮጀክቶች የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"ችግሩ ለአንድ ወገን  ከመስጠት ይልቅ እንደሀገር  በአፈጻም ዙሪያ ያሉብን ችግሮች በመፈተሽ የአፈጻጸም ስርአት መዘርጋት አለብን "ብለዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የፕሮጀክቶቹ መጓተት ሀገሪቱ በወቅቱ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ከማሳጣት ባለፈ እድገቷ በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይሄድና የፕሮጀክቶቹ ወጪም እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም